አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የወሰደችው አቋም “ኃላፊነት ጎደለው እና አደገኛ” ነው ሲሉ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ገለጹ፡፡

430
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የወሰደችው አቋም “ኃላፊነት ጎደለው እና አደገኛ” ነው ሲሉ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ላውረንስ ፍሪማን ይባላሉ፤ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኝ ናቸው፡፡ ከ30 ዓመታት በላይ በተለይ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲዎች ላይ ተሳትፎ አላቸው፡፡ ከሰሞኑ አሜሪካ ኢትዮጵያን በተመለከተ እያንጸባረቀቸው ያለውን አቋም በተመለከተ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ላውረንስ ፍሪማን ማብራሪያ ኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ጫና መዘዙ ለቀጣናው መትረፉ እሙን ነው፡፡ የሁለትዮሽ ብሎም የጋራ ጥቅምን ከግምት ውስጥ ያላስገባው የአሜሪካ ውሳኔ ለዓመታት የዘለቀውን የሀገራቱን ትብብር ወደኋላ የሚጎትት ብቻ ሳይሆን መላውን የአፍሪካ ቀንድን ብሎም አህጉሪቱን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ጸጥታና መረጋጋት እንዲሰፍን አይተኬ ሚና እንዳላት ተንታኙ ጠቅሰዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሊበራል ተቋማትን ለማስደሰት ተብሎ ብቻ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተስተዋለው የአሜሪካ አዲሱ አቋም “ኃላፊነት ጎደለው እና አደገኛ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡
አሜሪካ ለጠላቶቿ ያቀደቻቸውን እንደዚህ አይነት እርምጃዎች የረጅም ጊዜ ታማኝ አጋሮቿ ላይ እንደምትተገብራቸው ፍሪማን አንስተዋል፡፡የአሜሪካ እርምጃ ለጠላቶቿ የሳለችውን ሰይፍ ወዳጆቿ ላይ እንደ ማሳረፍ ተደርጎ ይወሰዳል ነው ያሉት፡፡
ፍሪማን ይሞግታሉ፤ ኢትዮጵያ በአሜሪካ የሥልጣን መንበር ላይ ሪፐብሊካኑም ሆኑ ዴሞክራቶቹ ቢፈራረቁ በምሥራቅ አፍሪካ ሽብርተኝነትን እና አክራሪነትን ለመዋጋት ከአሜሪካ ጋር ያለ ምንም አቋም መወላወል በብርቱ ተባብራለች፤ እናም ይህ አይነቱ ፊት ማዞር አይገባትም፡፡ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ የባይደንን አቋም መዛነፍ በተመለከተ በአንድ ወቅት በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የነበሩት ካሜሩን ሐድሰን “ይህ በአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ስትራቴጂካዊ ለውጥ ነው ፤ ለአሜሪካ ፍላጎቶች ትልቅ አቅም ከሆነ ሁኔታ ወደ ተቃራኒው የተደረገ ” ሲሉ መግለጻቸውን ፍሪማን ጠቅሰዋል፡፡
የባይደን አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አንቶኒ ብሊንከን እና የኮንግረንሱ ውሳኔ “ቂላቂል እና ፍትሐዊነት የጎደለው” ሲሉ ነው ፍሪማን የገለጹት፡፡ (እ.ኤ.አ.) በጥቅምት ወር 2011 የኦባማ አስተዳደር የሊቢያን መንግሥት ከስልጣን ለማውረድ የወሰነውን የተሳሳተ ውሳኔ ለማነጻጸሪያነት ጠቅሰዋል ተንታኙ፡፡ በዚህ ውሳኔ የተነሳ ሊቢያ እንደ ሀገር መቀጠል አቅቷት ሕዝቦቿ ለቀውስ መዳረጋቸውን እንዲሁም በቀጣናው የደረሰውን ምስቅልቅል መገንዘብ በቂ መሆኑን በማንሳት ይሞግታሉ ፍሪማን፡፡ እናም አሜሪካ ኢትዮጵያን በተመለከተ እያራመደች ያለችው አቋም የከፋ አህጉራዊ ቀውስ ያስከትላል ባይ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ኢኮኖሚያዊ ጫና እና ፖለቲካዊ መገለል ሕዝቡን የከፋ ሕይወት እንዲገፋ ከማድረጉም ባሻገር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡ “ጭካኔ የተሞላበት” ሲሉ የገለጹት የአሜሪካ ውሳኔ የፌደራል መንግሥቱ ላይ ጫና በማሳደር ለጽንፈኞቹ ሴራ እድል መስጠትም እንደሆነ ተንታኙ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ላይ እኩይ ዓላማ ያነገቡ እና በዙሪያዋ ያሰፈሰፉ በርካቶች መኖራቸውን የገለጹት ፍሪማን መዘዙ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም የሚተርፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ለአሜሪካ ፍላጎትም አይበጅም ባይ ናቸው፡፡ የጦርነት አስከፊነትን የገለጹት ተንታኙ በትግራይ ክልል አሸባሪው ትህነግ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን፤ ይህንን ቡድኑ እያመነ ኀላፊነት የጎደላቸው ዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ሲያስተባብሉ መስተዋላቸውን አንስተዋል፡፡
ፍሪማን የፌዴራሉ መንግሥት አሸባሪው ሕወሓት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሲፈጽም ዝም ብሎ መመልከት እንደሌለበት እና የተወሰደው ሕግ የማስከር ዘመቻ ምክንያታዊ መሆኑን አንስተዋል፡፡ (እ.ኤ.አ.) ሚያዝያ 12 እስከ 13/ 1861 ለአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ጅማሮ የነበረውን እና በአሜሪካ የደቡብ ካሮላይና ሚሊሻ በቻርለስተን አቅራቢያ በሚገኘው በአሜሪካን የጦር ሠራዊት ላይ የሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አብርሃም ሊንከን ጦሩ ራሱን እንዲከላከል ማዘዛቸውን በትግራይ ክልል ከተወሰደው እርምጃ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ራሱን ከአሸባሪው ጥቃት የመከላከል እና ሀገሪቱን ከጥፋት የመታደግ ሙሉ ኀላፊነት እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ምንም አማራጭ አልነበረም ብለዋል፡፡
አሜሪካ አሁን እያንጸባረቀች ያለው አቋም ላይ ለመድረስ በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ የሐሰት ዘገባ በሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛ መረጃ ላይ ተንተርሳ መሆኑን ነው ተንታኙ ያብራሩት፡፡ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር እንደመሆኗ መጠን የአሜሪካ ውሳኔ ይህንን ባከበረ መልኩ ሊሆን ይገባል ባይ ናቸው፡፡
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኩር ጋዜጣ ግንቦት 16/2013 ዓ.ም ዕትም
Next articleጉንቤት 15 ጌርክ 2013 ም. አሜቱ እትሜት (አሚኮ)