በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ምርጫ ቦርድ ገለጸ፡፡

284
በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ምርጫ ቦርድ ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ የሕግ ማዕቀፍ እና የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን በተመለከተ በ6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለሚሳተፉ ሴት እጩ ተወዳዳሪዎች በባሕር ዳር ስልጠና እየተሰጠ ነው። ከብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ ሀረገወይን ይመር ከዚህ በፊት በነበሩት ምርጫዎች በትኩረት ማነስ እና በአመለካከት ችግሮች የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ ቢሆንም በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የተሻሉ ዕጩ ተወዳዳሪዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኀበራዊ ጉዳዮች ተወክለው ሀሳቦቻቸውን እንዲያንጸባርቁ ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባልም ብለዋል። ሴቶች በፓለቲካው መሥክ ውክልና እንዲያገኙ ማድረግ ለሌሎች ሴቶች ድምጽ ከመሆን አልፎ ለቀጣይ ትውልድ ዓርአያ እንደሚኾኑም ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የእናት ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ ትዕግስት እምቢበል እንዳሉት ሴቶች ካላቸው ቁጥር አኳያ ተሳትፎውን ማሳደግ እንደሚገባ መክረዋል። ሴቶች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው እንዲያዩ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸውም አንስተዋል። ስልጠናው የዕጩዎችን አቅም እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥርተ ፆታ ትምህርት እና ማኀበራዊ አካታችነት ባለሙያ ጥበቡ አለፋቸው በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ቦርዱ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ብሎም ለመገናኛ ብዙኀን፣ ለምርጫ ታዛቢዎች እንዲሁም ለጸጥታ አካላት የምርጫውን አሳታፊነት አስመልክቶ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
ቦርዱ ሀገር አቀፍ የሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የጋራ ምክር ቤት ለመመሥረት በሂደት ላይ እንደሚገኝም አቶ ጥበቡ ገልጸዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሥልጠናም በሰብዓዊ መብቶች፣ በፆታ እኩልነት እና የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ፣ በቀጣናዊ እና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች፣ በኢትዮጵያ የምርጫ የሕግ ማዕቀፍ እና አሳታፊነት ላይ ትኩረት ይደረጋል ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአፍሪካዊያን ፖሊሲ አውጭዎች በመረጃ መረብ ደኅንነት ላይ በትብብር እንዲሠሩ ኢትዮጵያ ጠየቀች፡፡
Next articleበኩር ጋዜጣ ግንቦት 16/2013 ዓ.ም ዕትም