አፍሪካዊያን ፖሊሲ አውጭዎች በመረጃ መረብ ደኅንነት ላይ በትብብር እንዲሠሩ ኢትዮጵያ ጠየቀች፡፡

113
አፍሪካዊያን ፖሊሲ አውጭዎች በመረጃ መረብ ደኅንነት ላይ በትብብር እንዲሠሩ ኢትዮጵያ ጠየቀች፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) 10ኛው ዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ ደኅንነት ስብሰባ በበይነ መረብ እየተካሄደ ነው፡፡ ስብሰባው በመረጃ መረብ ደኅንነትና የዲጂታል ጠላፊዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየመከረ ነው፡፡
የኢፌዴሪ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) አፍሪካ በበይነ መረብ ግንኙነት ተደራሽነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ብትሆንም በመረጃ መረብ መንታፊዎች በአመት እስከ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር እንደምታጣ ተናግረዋል፡፡ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት በ469 ሚሊየን ገደማ የሞባይል መጠቀሚያዎች 456 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ዝውውር እንደሚፈፀም አብራርተዋል፡፡ እያደገ የመጣው የሞባይል የገንዘብ ዝውውር የመረጃ መረብ መንታፊዎች ዓይን ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል ነው ያሉት በማብራሪያቸው፡፡
አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ድርጅቶች የመረጃ መረብ ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዳልሆነና የፖሊሲ አውጭዎች በትኩረትና በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የበይነ መረብ ግንኙነት እየጨመረ መምጣት፣ በመረጃ መረብ ደኅንነት ላይ በቂ ግንዛቤ አለመኖር፣ ዝቅተኛ የዲጂታል እውቀት፣ የመረጃ መረብ ጥበቃ ባለሙያ እጥረት፣ ፍቃድ የሌላቸው ሶፍትዌሮችን መጠቀም የአፍሪካን የመረጃ መረብ ለመንታፊዎች እንዲጋለጥ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካን የበይነ መረብ ደኅንነት ለማስጠበቅ ከአፍሪካ 2063 አጀንዳ ጋር በተጣጣመ መልኩ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችንም ዶክተር አሕመዲን አስረድተዋል፡፡
በሂደት ላይ ያለው የአፍሪካ የአይ. ሲ. ቲ እድገት ሕግና ፖሊሲ፣ የኢንተርኔት ሰነድ፣ የመረጃ መረብ ደኅንነትና የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ (ማላቦ ኮንቬንሽን) እንዲሁም የመረጃ ደኅንነት ዳሰሳ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን እንደገለጹ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ዓለም አቀፉ የመረጃ መረብ ደኅንነት ስብሰባ ትኩረቱን የመረጃ መረብ ደኅንነት ላይ አድርጎ በየዓመቱ የሚካሄድ ስብሰባ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአዊኛ እና ኽምጣና ቋንቋዎች የቴሌቪዥን የአየር የሰዓት ማሻሻያ ማድረጉ ለቋንቋዎቹ እድገት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብረሃም አለኸኝ ገለጹ፡፡
Next articleበቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ምርጫ ቦርድ ገለጸ፡፡