
ኢትዮጵያ በሕግ ማስከበር እርምጃው የኬሚካል ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች በሚል የተሰራጨው መረጃ መሰረተ ቢስ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ስምምነት በተከለከለው የኬሚካል ጦር መሳሪያ ተጎጅ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ናት፡፡ ጣሊያን በዓድዋ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀል ለ40 ዓመታት ተዘጋጅታ ለዳግም ጦርነት ድንበር ጥሳ ገባች፡፡ ኢትዮጵያዊያንም ለሀገራቸው ክብር እና ሉዓላዊነት መከበር ወራሪውን ጦር ፊት ለፊት ተጋፈጡት፡፡ ነገር ግን የጦርነቱን ታሪክ ከቀየሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊያን አይተውት እና ሰምተውት የማያውቁትን የኬሚካል ጦር መሳሪያ የጣሊያን ጦር መጠቀሙ ነበር፡፡ በወቅቱ የኬሚካል ጦር መሳሪያ የተጠቀመውን የጣሊያን ጦር አስመልክቶ ኢትዮጵያ በዓለም የፍትህ አደባባይ አቤት ብትልም ሰሚ አላገኘችም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ አስከፊ ጉዳት ያደረሰባትን የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ እንዳይውል የቀረበውን ስምምነት ስትፈርም ዓላማዋ ቢያንስ በሀገሯ ጥቅም ላይ እንደማይውል እርግጠኛ በመሆን ነው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ዛሬ መቀመጫውን ኬኒያ ናይሮቢ ያደረገው የቴሌግራፍ መጽሔት የአፍሪካ ወኪል ዘጋቢ ዊል ብራውን ኢትዮጵያ በሕግ ማስከበር እርምጃው የኬሚካል ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች ሲል ያቀረበው መረጃ ስህተት መሆኑን ገልጿል፡፡ የሚኒስቴሩ ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት በሰጠው መግለጫ መጽሔቱ በትግራይ ክልል በተካሄደው ሕግ የማስከበር እርምጃ የኬሚካል ጦር መሳሪያ በመጠቀሙ ንጹሐን ላይ ጉዳት ደርሷል ሲል ሐሰተኛ መረጃ አሰራጭቷል ብሏል፡፡ ውንጀላው መሰረተ ቢስ እና ሐሰተኛ መሆኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ስምምነት የተከለከለውን የኬሚካል ጦር መሳሪያ በሕዝቦቿ ላይ አትጠቀምም፤ አልተጠቀመችምም ነው ያለው መግለጫው፡፡ ኢትዮጵያ ለፍትሕ እና ለሕግ ተገዥ በመሆኗ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተከለከለውን የኬሚካል ጦር መሳሪያ በሕግ ማስከበር እርምጃው የምትጠቀምበት ምንም አይነት ምክንያት አለመኖሩን አስታውቋል፡፡
በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የተሳሳተ እይታ እንዲኖር መሰል ኃላፊነት የጎደላቸው እና የተሳሳቱ መረጃዎች እየተሰራጩ መሆናቸውን ቀድሞ እንደገለፀ ያሳወቀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ይህም በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ውጥረቶችን ለማባባስ ያለመ ነው ብሏል፡፡ በተለያዩ አካላት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል አንዱ ነውም ብሏል፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ