ማሳን በኖራ በማከም የአርሶ አደሮችን ምርት ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

348
ማሳን በኖራ በማከም የአርሶ አደሮችን ምርት ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ለእርሻ ከሚውለው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታሩ አሲዳማ መሆኑን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ በተያዘው ዓመት 10 ሺህ ሄክታሩን አሲዳማ መሬት በኖራ ለማከም እየተሠራ ነው፡፡
አርሶ አደር ጌትነት ባለው በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ ፈርጥአጋማ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ በርበሬ፣ ዳጉሳ፣ በቆሎ እና ጤፍ በብዛት ያመርታሉ፡፡ አርሶ አደር ጌትነት በተደጋጋሚ በርበሬ የሚያመርቱበት መሬታቸው ምርቱ እየቀነሰ በመሄዱ ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡ የማሳው አሲዳማነት እየጨመረ መምጣቱን ቆይተውም ቢሆን ከባለሞያዎች የተረዱት አርሶ አደሩ ለችግሩ መፍትሄ ወደ ማፈላለግ ገቡ፡፡
በ2012 ዓ.ም ከግብርና ባለሙያዎች በተደረገላቸው ድጋፍ መሬታቸውን በኖራ በማከማቸው ምርታቸው የተሻለ እንደሆነም ከአሚኮ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደር ጌትነት መሬቱ በአሲድ በመጠቃቱ በርበሬው ካደገ በኋላ የመጠውለግ እና መልኩም ወደ ቢጫነት ይቀየር እንደነበረ ገልጸዋል፡፡ ከግማሽ ሄክታር መሬት ያገኙት የነበረው ምርትም 4 መቶ ኪሎ ግራም ያህል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ማሳው በኖራ በታከመበት 2012 ዓ.ም ግን 700 ኪሎ ግራም ማምረት ችለዋል፡፡ ሌሎች አርሶ አደሮችም መሬታቸውን ለማከም ኖራ እንዲጠቀሙ መክረዋል፡፡
ወጣት ታዘብ አንማው በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ነዋሪ ነው፡፡ ወጣት ታዘብ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሠብሎችን ያመርታል፡፡ በቂ መሬት ባለመኖሩም በማሳው ላይ ተመሳሳይ ሠብሎችን ያመርት ነበር፡፡ በዚህም የሚያገኘው ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠኑ እየቀነሰ በመሄዱ ችግር ገጥሞት ነበር፡፡ ከአንድ ሄክታር መሬት ከ20 እስከ 25 ኩንታል ምርት ብቻ ነበር የሚያገኘው፡፡
በ2012/13 የምርት ዘመን ከግብርና ባለሞያዎች ባገኘው ሙያዊ ድጋፍ መሬቱን በኖራ በማከሙ ከግማሽ ሄክታር መሬት 30 ኩንታል ምርት ማምረት መቻሉን ከአሚኮ ጋር በነበረው የስልክ ቆይታ ተናግሯል፡፡ ወጣት ታዘብ ኖራው ዝናብ በሌለበት ወቅት ማሳው ላይ በመነስነስ ከአፈሩ ጋር በማቀላቀል እየተጠቀመ እንደሆነም አብራርቷል፡፡ ወጣት ታዘብ ኖራ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀሙ 10 ኩንታል ያመተርትበት የነበረው ማሳ ከ60 እስከ 70 ኩንታል ድንች እያመረተ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙም ምክር እየሰጠ ነው፡፡ እስካሁን ኖራ ይቀርብ የነበረ በነፃ ቢሆንም በዚህ ዓመት ክፍያ ቢጠየቁም መጠቀሙን እንደማያቆም ነግሮናል፡፡ ወጣቱ እንዳለው መሬቱን ወደ ነበረበት ምርታማነት ለመመለስም አቅሙ በፈቀደ መጠን ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ እየተጠቀመ ነው፤ ሌሎች ይህን መንገድ እንዲከተሉም መክሯል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻል ባለሙያ አቶ አብዮት መኮንን እንዳሉት፡
• በአማራ ክልል ከሚገኙ 9 ዞኖች ውስጥ የሚገኙ 87 ወረዳዎች በአሲዳማነት የተጠቁ ናቸው፡፡
• በዘር ከሚሸፈነው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያየ ደረጃ በአሲዳማነት ተጠቅቷል፡፡
• በዚህ ዓመት 200 ሽህ ኩንታል ኖራ በማቅረብ 10 ሽህ ሄክታር መሬት በኖራ ለማከምም እቅድ ተይዟል፡፡
• ኖራውን ገዝቶ ለማምጣት ክልሉ 100 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
• በኖራ የታከመ መሬት ከ50 በመቶ እስከ 100 በመቶ ጭማሪ ሊያሳይ ይችላል፡፡
እንደ አቶ አብዮት ገለጻ የአፈር አሲዳማነት የሚከሰተው በረጅም ጊዜ የተፈጥሮ መዛባት፣ የተዛባ የመሬት አጠቃቀም እንዲሁም በተፈጥሮ የሚከሠት በመሆኑ ችግሩን በቀላሉ መቅረፍ አስቸጋሪ ነው፡፡ ችግሩን መለየትና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የተሠጠው ትኩረት አናሳ መኾን፣ ሥራው ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት የሚጠይቅ መኾን፣ ኖራውን ለመነስነስና ከአፈር ጋር ለማደባለቅ ተግባራዊ የሚደረገው በባሕላዊ ዘዴ መኾኑ ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ እንዳይሠጠው አድርጎታል ብለዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት 5 ሺህ 815 ሄክታር መሬት ብቻ ነው በኖራ ማከም የተቻለው፡፡ በክልሉ የኖራ አምራች ፋብሪካዎች ቁጥር አናሳ በመሆኑ ሌሎች ፋብሪካዎች እንዲያመርቱ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም በርብርብ መሠራት አለበት ነው ያሉት፡፡ ማሳን በኖራ ማከም ከምርት የወጡ ማሳዎችን ወደ ማምረት የመመለስ አቅም ያለው መሆኑንም ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡
አቶ አብዮት እንዳሉት መንግሥት የቴክኖሎጅውን አዋጭነት ለማስተዋወቅ ኖራን በድጎማ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ይህ ሥርዓት የማይቀጥል በመሆኑ አርሶ አደሩ ገዝቶ የመጠቀም ልምዱን ሊያዳብር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የኖራ ድልድሉም እንደ አፈሩ የጉዳት መጠን የተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መግዛት ለማይችሉ አርሶ አደሮችም ብድር ተመቻችቷል ነው ያሉት፡፡ ባለሙያው እንዳሉትም ጥራቱን የጠበቀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ መጠቀም በአሲድ የተጠቃን ማሳ ከሦስት ዓመታት እስከ አምስት ዓመታት ድረስ ለማከም ድርሻው የጎላ ነው፡፡
ችግሩ ከዚህ የባሠሰ ጉዳት እንዳያስከትል የአፈር እና የውኃ እቀባ ሥራን አጠናክሮ መሥራት፣ አረንጓዴ ማዳበሪያ መጠቀም፣ ሠብልን በፈረቃ መዝራት እና ተረፈ ምርትን መጠቀም እንደሚገባ ባለሙያው መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በኽምጣናና አዊኛ ቋንቋዎች ዕለታዊ የቴሌቪዥን ሥርጭት ጀመረ፡፡
Next articleኢትዮጵያ በሕግ ማስከበር እርምጃው የኬሚካል ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች በሚል የተሰራጨው መረጃ መሰረተ ቢስ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡