
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በኽምጣናና አዊኛ ቋንቋዎች ዕለታዊ የቴሌቪዥን ሥርጭት ጀመረ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከግንቦት 16/2013 ዓ.ም ጀምሮ በኽምጣናና አዊኛ ቋንቋዎች ከሰኞ እስከ አርብ የ30 ደቂቃ ዕለታዊ የቴሌቪዥን ሥርጭት ጀመሯል። በዚህም መሰረት ኽምጣና ቋንቋ ከሰኞ እስከ አርብ ከቀኑ 7:00 እስከ 7: 30 እንዲሁም አዊኛ ቋንቋ ደግሞ ከሰኞ እስከ አርብ ከቀኑ 7:30 እስከ 8:00 ስርጭታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡
የኽምጣናና አዊኛ ቋንቋዎች የቴሌቪዥን ዝግጅት ክፍሎች ከአሁን ቀደም በሳምንት የአንድ ሰዓት ስርጭት ነበራቸው። ከዛሬ ጀምሮ ከሰኞ እስከ አርብ የ30 ደቂቃ ስርጭት እንዲኖራቸው መወሰኑን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን ሰጥዬ እንደተናገሩት ዕለታዊ የቴሌቪዥን ሥርጭቱ ብሔረሰቦች ቋንቋቸውንና ባሕላቸው እንዲያድግ ያስችላል፤ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትም ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም አስገንዝበዋል።
ኮርፖሬሽኑ ያደረገው ዕለታዊ የቴሌቪዥን ሥርጭት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ለማሳደግና ለማስተሳሰር ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋልም ብለዋል። የቋንቋዎቹ ተናጋሪዎች በዝግጅቶቹ በመሳተፍ የሚጠበቅባቸውን ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
“የቋንቋዎቹ ተናጋሪዎችም የመረጃ ምንጭ በመሆንና ገንቢ ሀሳብ በመስጠት ሊሳተፉበት ይገባል” ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ።
ኮርፖሬሽኑ የኹለተኛ ጣቢያ ስርጭት ሲጀምር ቋንቋዎቹ ተጨማሪ የአየር ሰዓት እንደሚያገኙም አስታውቀዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በብሔረሰብ ቋንቋዎች በቴሌቪዥን፣ በራድዮ፣ በጋዜጣና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ኅብረተሰቡን እያገለገለ እንደሚገኝም ዋና ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
የቀድሞው የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ እና የአማራ ክልል የእጽዋት ዘርና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ኳራንታይን ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ደባሱ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ማኅበረሰብ የተደረገለትን የሰዓት ማሻሻያ ተጠቅሞ የመረጃ ምንጭ በመሆን፣ ገንቢ ሀሳብን በመስጠት ሊደግፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አቶ ሙሉጌታ ኮርፖሬሽኑ ላደረገው ዕለታዊ የቴሌቪዥን ሥርጭት ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ኮርፖሬሽኑ ከሚያዝያ 25/2013 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮምኛ ቋንቋ ዝግጅት ክፍል ሲያሰራጭ የነበረው የአየር ሰዓት ላይ ማሻሻያ ማድረጉና የትግርኛ ቋንቋ ዝግጅት ማስጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ