በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እና መልሶ ማቋቋም ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

159

በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እና መልሶ ማቋቋም ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን እዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ በከፈተው ጥቃት ነበር
መንግሥት ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ የገባው። ይህም መንፈቅ ዓመት ሊሞላው ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው በአሸባሪው ሕወሓት የተፈጸመው ወንጀል የሀገርን አንድነት የሚፈታተን በመሆኑ መንግሥት
ይህንን ለመቀልበስ ወደ ዘመቻው ገብቷል፡፡ ይህም ሀገሪቱን ዋጋ አስከፍሏታል፤ በተለይ ደግሞ የትግራይ ሕዝብን። ሕይወት
ተቀጥፏል፤ ሕይወት ተመሰቃቅሏል፤ ሺህዎችንም በአካልም በስነልቦናም ጫና አሳድሯል፡፡
በትግራይ ክልል ችግሮች እንዳይባባሱ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ፣ ሕዝቡ ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስ በማድረግ እና
መሠረተ ልማቶችን መልሶ በማቋቋም ረገድ መንግሥት ባለፉት በርካታ ሳምንታት ተቋማዊ በሆነ መልኩ ወሳኝ እርምጃዎችን
ወስዷል ብሏል፡፡
የሰብዓዊ ድጋፍ ማእከላት ክፍት ተደርገው የምግብ፣ የመድኃኒት እና የአሰቸኳይ ጊዜ ድጋፎች ተደርገዋል፡፡ ለድጋፍ ሰጪ አካላት
አስተማማኝ ጥበቃ ማድረግ፣ የቆይታ ፈቃዳቸውን ማራዘም፣ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራም ተከናውኗል ነው ያለው፡፡
በቅርቡ ደግሞ የበረራ መስመሮች ክፍት መደረጋቸውን ጠቅሷል፡፡ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ የሚያሰባሰብ
የመንግሥት፣ የምሁራን ፣ የሃይማኖት አባቶች እና የንግድ ማኅበረሰብ አባላትን ያቀፈ የጋራ ኮሚቴ መቋቋሙን ሚኒስቴሩ
አስታውቋል፡፡
የሰብዓዊ ድጋፉ እንዳይሰተጓጎል ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ነው ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡ የፌዴራል መንግሥት በክልሉ የሰብዓዊ
ጥሰቶችን በማጣራት ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ ቁርጠኛ መሆኑን ነው መግለጫው በአጽንኦት የገለጸው፡፡
ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛ ሚና አክብሮት እንዳለው የገለጸው መግለጫው የብዙኃን መገናኛዎች
ባልደረሱባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የትክክለኛ መረጃ ክፍተት መኖሩን ጠቅሷል፡፡ በዚህም ያልተረጋገጡ መረጃዎች በማኅበራዊ
የትስስር ገጾች እንዲንሸራሸሩ አድርጓል፡፡ የመረጃ ክፍተቱን በመጠቀም የሐሰት መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት ጉዳዩን እንደ
መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ለራሳቸው ዓላማ እንደሚጠቀሙበት እንገነዘባለን ብሏል ሚኒስቴሩ።
በቅርቡ አንድ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ህትመት በቀጣዮቹ ቀናት ይዞት በሚወጣው ዘገባ ላይ በክልሉ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቅም
ላይ ውሏል የሚል የሐሰት ዘገባ እንደሚያወጣ መረጃ እንደደረሰው ሚኒስቴሩ አመላክቷል፡፡ ክሱ ተንኮል አዘል እና ኀላፊነት
የጎደለው ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ክሱ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት በሚደረግበት በዚህ ወቅት ሀገር ለመከፋፈል እና ተጨማሪ ችግር ለመፍጠር ያለመ ነው
ብሏል፡፡
መንግሥት ክፍት የተደረጉ የሰላም ፣ የውይይት እና የብሔራዊ እርቅ በሮች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ባሉ አካላት ትንኮሳ
እንዲዘጉ አይፈቅድም ነው ያለው መግለጫው፡፡
መግለጫው መንግሥት ዴሞክራሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን መገንባቱን ይቀጥላል፤ የለውጥ ማሻሻያ አጀንዳዎቹን
ያከናውናል ብሏል፡፡
ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየአማራ ሕዝብ የተጋረጡበትን ችግሮች ከሕዝብ ጋር በመተባበር ለመፍታት እንደሚሠራ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ገለጸ፡፡
Next articleባለፉት ሦስት ዓመታት 56 ሽህ 790 የከተማና የገጠር ውኃ ተቋማት ግንባታ በማጠናቀቅ ከ15 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎችን የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡