
“የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን ለማድረግ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ድርሻ አለው” የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የድሮን ጉባዔ 2021 ላይ በክብር ተጋባዥነት እየተሳተፈች ነው።
የዘንድሮው “5ኛው አለም አቀፍ የሰው አልባ አውሮፕላን ጉባዔ 2021” በቻይና ሸንዠን እየተካሄደ ነው።
በቻይና የጓንዡ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል አምባሳደር እውነቱ ብላታ የሰው አልባ አውሮፕላንና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ትልቅ አቅም እየፈጠረ ነው ብለዋል።
ቴክኖሎጂው በአቪየሽን፣ በጤና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ግብርና፣ አረንጓዴ ልማት፣ የመሬት አስተዳደርና የማዕድን ዘርፍ ውስጥ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ አምባሳደሩ በኢትዮጵያና ቻይና ተቋማት መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) “በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ ውስጥ የተካተተውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን ለማድረግ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ድርሻ አለው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማሳደግና የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታዋን ለማፋጠን የድሮን ሕግ ማውጣቷንና የጀማሪ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች በሰው አልባ አውሮፕላን ቴክኖሎጂ ዘርፍ እንዲሰማሩ አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠረች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቻይና አፍሪካ ጥምረት በኩል ያለው የኢትዮ ቻይና ግንኙነትም ከቻይና የአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በጉባዔው ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ የኢንደስትሪና ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ የተቋም መሪዎችና ምሁራን እየተሳተፉ እንደሚገኝ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
የቻይናና የውጭ ሀገራት ድርጅቶ ከ200 በላይ የዘርፉን አዳዲስ ምርቶች ይዘው ቀርበዋል።
ኢትዮጵያ፣ ስዊዘርላንድና ፓኪስታን በጉባዔው የክብር ተጋባዥ ሀገራት ናቸው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ