
“ኢትዮጵያን ለማዳከምና አንድነቷን ለማናጋት ከየትኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ አካል የሚሰነዘር ትንኮሳ እና ጫና ለመመከት እንሠራለን” ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ-ኢትዮጵያውያን ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ እንዳሉት በአሜሪካ የሚኖሩ ዲያስፖራዎች ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ እየወሰዱት ያለውን ያልተገባ ተጽእኖ ለመቋቋም በላቀ አንድነትና ቅንጅት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ሀገሪቱን ለማዳከምና አንድነቷን ለማናጋት ከየትኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ አካል የሚሰነዘር ትንኮሳ እና ጫና ለመመከት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ከውይይቱ በኋላ ባወጡት የአቋም መግለጫ
ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃገብነትን ፈጽሞ የማትቀበል ሉዓላዊ ሀገር እንደመሆኗ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ መንግሥት በኩል የሚደረገዉ ፍትሐዊ ያልሆነ ጫና በአስቸኳይ እንዲቆም እና የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማክበር በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ከመግባት እንዲታቀብ ጠይቀዋል፡፡
የአሸባሪው ሕወሓት ርዝራዦችና ተላላኪዎች ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበር የሀገሪቱን ስም የሚያጠለሹና የተሳሳቱ መረጃዎችን በመገናኛ ብዙኃን በስፋት በማሰራጨት የሚያደርጉትን የሐሰት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለማጋለጥ እንሠራለን ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እና የሁለተኛዉ ዙር የውኃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ ዉስጥ እንዳይሳካ ለማደናቀፍና ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሠሩ ኃይሎች በእጅ አዙር የሚያደርሱትን ጫና አጥብቀን እንቃወማለን፤ ይህንንም ጫና ለመመከት እስከመጨረሻዉ ድረስ በጋራ እንቆማለን ነው ያሉት፡፡
የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናትን፣ የኮንግረስ አባላት እና ሴናተሮች በኢትዮጵያ ያለዉን ትክክለኛ ገፅታ እንዲገነዘቡ እና በሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመመራት የተሳሳተ አቋም እንዳያራምዱ በማድረግ፣ ሰሞኑን የአሜሪካ ሴኔት ያወጣውን ሪዞሊሽን መልሶ እንዲያጤነው እና የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ እንዲሆን ጠንክረው እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ በመላክ እና በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሳተፍ የኢትዮጵያን ልማት ለመደገፍ ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ እንደሚያርጉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ወደ ማገባደጃ ምእራፍ በተቃረበችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ሆን ተብሎ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ እና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በውጭና በሀገር ውስጥ የጥፋት ኃይሎች የሚደረገዉን ዘመቻ ለመመከት አንድነታችንን አጠናክረን ከመቼዉም ጊዜ የበለጠ በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን በመግለጫቸው እንዳመላከቱ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ