ቦርዱ ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ 106 ሺህ 345 ምርጫ አስፈጻሚዎችን መልምሎ እንደሚያሰለጥን ገለጸ።

366

ቦርዱ ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ 106 ሺህ 345 ምርጫ አስፈጻሚዎችን መልምሎ እንደሚያሰለጥን
ገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የተለያዩ
ዝግጅቶቸን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል።
ግንቦት 7/2013 ዓ.ም ቦርዱ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ምክክር የድምፅ መስጫ ቀን በታቀደለት ግንቦት 28 እና ሰኔ
5/2013 ዓ.ም መከናወን እንደማይችል በተጨማሪ ከ2 እስከ 3 ሳምንት ዝግጅት ጊዜ እንደሚያስፈልግ መግለጹን አስታውሷል።
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ከሚገኙት 138 ሺህ 655 የምርጫ አስፈጻሚዎች በተጨማሪ በመጪዎቹ ቀናት 106 ሺህ 345
ምርጫ አስፈጻሚዎችን መልምሎ እንደሚያሰለጥን የገለጸው ቦርዱ ከእነዚህ መካከል በቦርዱ መጠባበቂያ ዝርዝር ላይ ተጨማሪ
100 ሺህ 333 አስፈጻሚዎች አሉ ብሏል።
ከእነዚህ ተጨማሪ ምርጫ አስፈጻሚዎች በቦርዱ በተጠባባቂነት የተያዙ ሲሆን ቦርዱ መስፈርቱን የማጣራት እና የማሰልጠን ሥራ
አጠናቆ ለድምጽ መስጫ ቀን ዝግጁ ያደርጋል ተብሏል።
እንዲሁም ከፍተኛ የአስፈጻሚ ቁጥር ክፍተት ባለባቸው ክልሎች በልዩ ሁኔታ ለመሙላት ጥረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል።
ለስልጠና ቁሳቁስ እሸጋ እና ስርጭት በአጠቃላይ አራት ቀናት ይፈጃል ያለው ቦርዱ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ከ10 ቀናት
በኋላ የሚጠናቀቅ ሲሆን ከዚያም በተጨማሪ የድምጽ መስጫ ወረቀት፣ ፎርሞች እና ከሌሎች ተገዝተው የተቀመጡ የድምፅ
መስጫ ቁሳቁስን በምርጫ ክልል አከፋፍሎ ማሸግ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ከተጠናቀቀ በኋላ አራት ሳምንታት
እንደሚፈጅ ተነግሯል።
ቦርዱ የትራንስፓርት እቅድ ያዘጋጀ ሲሆን ከመራጮች ምዝገባ ልምድ በመነሳት የፌዴራል ተቋማት፣ የክልል መንግሥታት እና
የሌሎች አካላት ከፍተኛ ትብብር ይጠይቃል ነው የተባለው።
ይህ የኦፕሬሽን ዝግጅትም ቦርዱ ሙሉ ኀይሉን አሟጦ በመጠቀም የሚከናወን መሆኑን አስታውቋል። በዚህም መሰረት 6ተኛው
አጠቃላይ ምርጫ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ይካሄዳል።
ነገር ግን ድምጽ የመስጠት ሂደቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከናወንባቸው የማይችሉ የምርጫ ክልሎች እና የምርጫ ጣቢዎች
እንደሚገኙ ነው ከቦርዱ የተገኘው መረጃ ያመላከተው። በእነዚህ አካባዎች ድምጽ የመስጠት ሂደቱ የማይከናወንባቸው
ምክንያቶች በጸጥታ ችግሮች የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው ቦታዎች፣ የመራጮች ምዝገባ ተጀምሮ የተቋረጠባቸው
ቦታዎች እና የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ አቤቱታ የቀረበባቸው ወይም ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ላይ ጉልህ የአሠራር
ችግር በማየቱ ማጣራት የወሰነባቸው ቦታዎች ናቸው ተብሏል።
በተለያዩ ምክንያቶች (በጸጥታ እና በመራጮች ምዝገባ አቤቱታ) ድምጽ የመስጠት ሂደቱ በሰኔ 14/2013 ዓ.ም ተግባራዊ
ሊሆን የማይችልባቸው የምርጫ ክልሎችንም ቦርዱ ለይቷል። እነዚህም:
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል (4 ምርጫ ክልል)
የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመባቸው ቦታዎች
1. መተከል ምርጫ ክልል
2. ሺናሻ ልዩ ምርጫ ክልል
3. ካማሽ ምርጫ ክልል
4. ዳለቲ ምርጫ ክልል
ሶማሌ ክልል (14 ምርጫ ክልል)
የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ አቤቱታ የቀረበባቸው እና የማጣራት ሂደቱ ላይ የሚወሰኑ
1. አራቢ የምርጫ ክልል
2. ደግሃመዶ ምርጫ ክልል
3. ጎዴ የምርጫ ክልል
4. ጂግጂጋ 1 የምርጫ ክልል
5. ጂግጂጋ 2 የምርጫ ክልል
6. ቀብሪደሃር ምርጫ ክልል
7. ቀላፎ ምርጫ ክልል
8. ዋርዴር ምርጫ ክልል
9. ፊቅ ምርጫ ክልል
10. ገላዲን ምርጫ ክልል
11. ደገሃቡር ምርጫ ክልል
የመራጮች ምዝገባ ሂደት በክልሉ መስተዳድር የተቋረጠባቸው
1. አይሻ ምርጫ ክልል
2. ኤረር ምርጫ ክልል
3. ሽንሌ ምርጫ ክልል
ኦሮሚያ ክልል (7 ምርጫ ክልል)
የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው (በጸጥታ ችግር)
1. ቤጊ ምርጫ ክልል – ምእራብ ወለጋ
2. ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል – ምእራብ ወለጋ
3. አያና ምርጫ ክልል – ምስራቅ ወለጋ
4. ገሊላ ምርጫ – ምስራቅ ወለጋ
5. አሊቦ ምርጫ ክልል -ሆሮ ጉድሩ
6. ጊዳም ምርጫ ክልል- ሆሮ ጉድሩ
7. ኮምቦልቻ ምርጫ ክልል- ሆሮ ጉድሩ
አማራ ክልል (8 ምርጫ ክልል)
የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው (በጸጥታ ችግር)
1. ማጀቴ (ማኮይ) ምርጫ ክልል
2. አርጎባ ልዩ ምርጫ ክልል
3. ሸዋሮቢት ምርጫ ክልል
4. ኤፌሶን ምርጫ ክልል
5. ጭልጋ 1 ምርጫ ክልል
6. ጭልጋ 2 ምርጫ ክልል
7. ላይ አርማጭሆ ምርጫ ክልል
8. ድልይብዛ ምርጫ ክልል
ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል (4 ምርጫ ክልል)
የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው (በጸጥታ ችግር)
1. ዘልማም ምርጫ ክልል
2. ሱርማ ልዩ ምርጫ ክልል
3. ዲዚ ልዩ ምርጫ ክልል
4. ሙርሲ ልዩ ምርጫ ክልል
ሐረሪ ክልል (3 ምርጫ ክልል)
የመራጮች ምዝገባ ከፍተኛ የተዛባ አሠራር የታየባቸው እንዲሁም በሕግ የተያዘ ጉዳይ
1. ጀጎል ልዩ ምርጫ ክልል
2. ጀጎል መደበኛ ምርጫ ክልል
3. ጀጎል ዙሪያ እና ሁንደኔ ምርጫ ክልል
ቦርዱ በልዩ መግለጫነትም በጋምቤላ ክልል ዲማ ምርጫ ክልል እና አኮቦ ምርጫ ክልል ከፍተኛ የመሰረተ ልማት እና የመጓጓዥ
ችግር በመኖሩ በልዩ ሁኔታ የክልል እና የፌደራል መንግሥትን ከፍተኛ እገዛ እንደሚጠይቁ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“አሸባሪው ሕወሃት በመወገዱ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በስሙ የተነገደበት የትግራይ ሕዝብም ነፃ ወጥቷል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው
Next article“ኢትዮጵያን ለማዳከምና አንድነቷን ለማናጋት ከየትኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ አካል የሚሰነዘር ትንኮሳ እና ጫና ለመመከት እንሠራለን” ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን