ለሰላም ግንባታና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሀገር በቀል እውቀት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመላከተ፡፡

170
ለሰላም ግንባታና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሀገር በቀል እውቀት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመላከተ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና የሰላም ግንባታን ለማሳለጥ የሀገር በቀል እውቀት ሚና ቅኝት ላይ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት በወሎ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
6ኛው ዓለም አቀፍ የሀገር በቀል እውቀት አውደ ጥናት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም የባሕል እና ሀገር በቀል እውቀት ጥናት ባለሙያዎች በተገኙበት በወሎ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
በአውደ ጥናቱ የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ ሰይድ ሙሃመድ፣ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ሰላምና በሕዝቦቿ አንድነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ነባር እሴቶችና የሀገር በቀል እውቀቶች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቁመዋል። ወሎ እነዚህ መልካም ባህሎችና እሴቶች በስፋት የሚገኙበት መሆኑንም አንስተዋል።
የወሎ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አፀደ ተፈራ (ዶክተር) በወሎና አካባቢው አንድነትና ትብብርን የሚገልፁ፣ትውልድን በመልካም ሥነ ምግባርና እሴት የሚያንፁ የባህላዊ ሥርዓቶችና የሀገር በቀል እውቀቶች መገኛ መሆኑን ጠቁመዋል። የአውደ ጥናቱ ዋነኛ ዓላማም በነባር ባህሎችና ሀገር በቀል እወቀቶች ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ ጠቀሜታቸውን በማሳዬትና በማጉላት ተጠብቀው እንዲቆዩና ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ መሆኑን ዶክተር አፀደ ገልጸዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አፈወርቅ ካሱ (ፕሮፌሰር) በሀገሪቱ ቀጣይነት ያለው ልማትና እድገት ለማምጣት ለሀገር በቀል እውቀት የላቀ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋልም ብለዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም የሀገር በቀል እውቀቶች ላይ ጥልቅ ምርምርና ጥናት እንዲካሄድ የሀገር በቀል እወቀት መረጃ ማእከላት እንዲቋቋሙ በአፅንኦት ይሠራል ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ።
ይህን እውን በማድረግ ሂደትም የዩኒቨርስቲዎች ሚና የላቀ መሆኑን አስረድተዋል። በአውደ ጥናቱ ላይ በግብርና እና አካባቢ ጥበቃ፣ በሀገረሰባዊ መድኃኒት ቅመማ፣ በሀገር በቀል ትውፊታዊ ተቋማትና በሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥናትና ምርምሮች እንደሚቀርቡ ተመላክቷል።
ዘጋቢ፡- ጀማል ሰይድ -ከደሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ማንነት ከውስጥ የሰረፀ በጭቆና ብዛት የማይተውት በመደለያ ገንዘብና ጥቅማጥቅም የማይቀይሩት ነው” ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ
Next article“የትናንት ጠላቶች፣ ከውጭ ኀይሎች ጋር በመተባበር አማራን አንገት ለማስደፋት እየሠሩ ነው” የርእሰ መስተዳድሩ ልዩ አማካሪ ደሳለኝ አስራደ