“ማንነት ከውስጥ የሰረፀ በጭቆና ብዛት የማይተውት በመደለያ ገንዘብና ጥቅማጥቅም የማይቀይሩት ነው” ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ

308
“ማንነት ከውስጥ የሰረፀ በጭቆና ብዛት የማይተውት በመደለያ ገንዘብና ጥቅማጥቅም የማይቀይሩት ነው” ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ ነፃነት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በወፍ አርግፍ ከተማ የምስጋና እና የእውቅና ዝግጅት እየተካሄደ ነው። በእውቅና ዝግጅቱ ላይ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለየት ያለ ከአፓርታይድ አገዛዝ ከፍ ያለ ግፍና በደል ተፈፅሟል ነው ያሉት።
አሸባሪው ትህነግ በሕዝቡ ላይ ግልፅ ዘር ማጥፋት ፈፅሟልም ብለዋል። ከከፋኝ እስከ አሁኑ ትውልድ ድረስ በተደጋጋሚ ትግል ሀገራዊ ለውጥ እንዲመጣ ካስገደዱ አጀንዳዎች ውስጥ የወልቃይት ጠገዴ የነፃነት ጥያቄ አንዱ ነው ብለዋል።
ትህነግ ገና ከደደቢት በረሃ ሲነሳ በአማራ ጠል ትርክት የተነሳ መሆኑን ነው የተናገሩት። በተስፋፊነት ባሕሪው አካባቢውን በኀይል ይዞ የወልቃይት ጠገዴን ያልተነካ ሀብት ለመጠቀም ሲል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወገዘውን የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙንም አስገንዝበዋል።
ትህነግ የአማራን ማንነት ለማጥፋት ያልሞከረው ነገር እንደሌለም ተናግረዋል። “ማንነት ከውስጥ የሰረፀ በጭቆና ብዛት የማይተውት በመደለያ ገንዘብና ጥቅማጥቅም የማይቀይሩት ነው” ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ወልቃይቴው ለአማራነት ክብሩ መስዋዕትነት ከፍሏልም ብለዋል።
ህፃናት በቤተሰቦቻቸው ቋንቋ እንዳይናገሩና እንዳይማሩ ሲደረጉም መቆየታቸውን አስታውሰዋል። የትህነግ የመጨረሻው የጥፋት መርከብ በማይካድራ ላይ የፈፀመው የዘር ማጥፋት ቢሆንም የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ለዓመታት ብዙ ማይካድራዎችን አይቷል ነው ያሉት።
ትህነግን በተለያዩ የትግል ዘርፎች በመውጋት ድል መገኘቱንም ተናግረዋል። የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና መከላከያ ሠራዊት ባደረገው ተጋድሎ ነፃነት ተገኝቷልም ብለዋል። ወልቃይት ጠገዴ ቁልፍ የሀገሪቱ ሥፍራ መሆኑንም አንስተዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ነፃ እንዲወጣ ላደረጉ ሁሉም አመስግነዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ – ከወፍ አርግፍ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየዚህ ዓመት ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ ፋሲል ከነማ ዋንጫውን ተረከበ።
Next articleለሰላም ግንባታና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሀገር በቀል እውቀት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመላከተ፡፡