የዚህ ዓመት ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ ፋሲል ከነማ ዋንጫውን ተረከበ።

423
የዚህ ዓመት ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ ፋሲል ከነማ ዋንጫውን ተረከበ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አራት ጨዋታዎች እየቀሩት ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው ፋሲል ከነማ ዛሬ በ25ኛው ሳምንት ከሀዋሳ ከነማ ጋር ተጫውቶ በአቻ ውጤት አጠናቅቋል፡፡ ጎሎቹንም ለፋሲል ከነማ በ31ኛው ደቂቃ ዓለም ብርን ለሀዋሳ ከነማ በ95ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ አስቆጥረዋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም ከደቡብ አፍሪካ ተሰርቶ የሚመጣው ታሪካዊው ዋንጫ ለዛሬ ባለመድረሱ በጊዜዊነት የተዘጋጀውን ዋንጫ ከፍ አድርጓል። በዛሬው ጨዋታ በሁለቱም ክለቦች በኩል ደጋፊዎች በሃዋሳ ዩንቨርስቲ ስታዲየም የታደሙ ሲሆን የአፄዎቹ ደጋፊዎች ታሪካዊውን ድልና ደስታ ከቡድን አባላቱ ጋር አጣጥመዋል።
አሰልጣኝ ስዩም ከበደን ጨምሮ የቡድኑ አባላት እንዳሉት ፋሲል ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለዋንጫ ተቃርቦ በተለያዩ ምክንያቶች ዋንጫውን አጥቷል። አሁን ከብዙ ሥራና ድካም በኋላ ያሰበውን አሳክቷል ነው ያሉት። በድሉም መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ሊጉ በዲኤስ ቲቪ መተላለፍ በጀመረበት ዓመት ሻምፒዮን መሆናቸው ደግሞ የተለየ ስሜትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል። ሊጉ ከሀገሪቱ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመታየት እድል ስለነበረው በብቃታቸው አሳምነው ንፁህ ዋንጫ መውሰዳቸውን ነው የተናገሩት።
የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ከክለቡ ጋር ብዙ እንደደከሙ፣ ውጣ ውረዶችን እንዳዩ ገልፀው ይህ ዋንጫ ለነሱ ይገባቸዋል መታሰቢያነቱም ለክለቡ ሲሉ ህይወታቸው ላጡ ደጋፊዎች ይሁን ብለዋል። የፋሲል ትልቅነት በሀገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር በአህጉራዊ ውድድር የተሻለ ውጤት ያስፈልገዋል፤ በባለፉት ሁለት የካፍ ኮንፌዴሬሽን ውድድሮች ልምድ ማግኘታቸው ቀጣይ ኢትዮጵያን ወክለው በሚሳተፉበት የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ረዥም ርቀት ለመጓዝ እንደሚሠሩ ተጫዋቾችና አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ተናግረዋል።
ዓመቱን በወጥ ብቃት የተጫወተው ፋሲል ከነማ በውድድር ዓመቱ በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ተሸንፏል። ካደረጋቸው 23 ጨዋታወች በሁለተኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 3ለ1 ሲረታ ከ19 ጨዋታዎች በኋላ 24ኛው ሳምንት ላይ በድሬዳዋ ከተማ 3ለ2 ተሸንፏል። 16 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ በቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 53 ነጥቦችን ደግሞ ሰብስቧል። ባጠቃላይ 42 ግቦችን ሲያስቆጥር 17 ግቦች ተቆጥረውበታል። በሊጉ ብዙ ግቦችን በማስቆጠርም በኢትዮጵያ በቡና ብቻ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል።
ዘጋቢ፡- ባዘዘው መኮንን – ከሀዋሳ
ፎቶ፡ ከፋሲል ከነማ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበሶስቱ ሀገሮች ብሔራዊ ገለልተኛ የሳይንቲስቶች ቡድን ባዘጋጀው የውኃ ሙሌት መርሃ ግብር መሰረት የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት እንደሚካሄድ ተገለጸ።
Next article“ማንነት ከውስጥ የሰረፀ በጭቆና ብዛት የማይተውት በመደለያ ገንዘብና ጥቅማጥቅም የማይቀይሩት ነው” ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ