ኢትዮጵያዊያን “በውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ የተዘረጉ የውጭ እጆች ይነሱ” ሲሉ ጠየቁ።

125

ኢትዮጵያዊያን “በውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ የተዘረጉ የውጭ እጆች ይነሱ” ሲሉ ጠየቁ።
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2013 (አሚኮ) ኢትዮጵያዊያን የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በያሉበት ኾነው ድምፃቸውን
የሚያሰሙበት መርኃግብር በመላ ኢትዮጵያ ተካሂዷል።
“እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ” በሚል መሪ ሐሳብ በያሉበት ሆነው ለአንድ ሰዓት መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉበት መርኃ
ግብር በሀገር ፍቅር ቲያትር ቅጥር ግቢ በይፋ ተጀምሯል።
“ብሔራዊ ክብር ፣ በሕብር” የሚል ስያሜ ያለውን ይህን ንቅናቄ ያዘጋጁት የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ አርቲስቶች፣ የሲቪክ
ማኅበራትና ታዋቂ ግለሰቦች ናቸው።
“ግድቡ ገንዘቤ፣ ዓባይ ወንዜ!፣ ዓባይ ጸጋችን ነው፣ ኢትዮጵያ አትደፈርም አንንበረከክም” የሚሉ መፈክሮችንም አስተጋብተዋል።
“ክብርና ሉዓላዊነታችንን አትንኩ የምንለው በአያቶቻችንን መስዋዕትነት የታፈረች፣ የተከበረች እና በዋጋ የተረከብናት አገር
በመሆኗ ነው” ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል አዘጋጆቹ።
የንቅናቄው መልዕክት በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች ተላልፏል።
“ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ነፃነትን ያስተማረች፤ አልገዛም ባይነትን በተግባር ያሳየች፤ የነፃነት ተምሳሌት ሀገር ነች” ሲሉም
ተናግረዋል።
“ከአያቶቻችንና የወረስነው ልበ ሙሉነት፣ ሌላውን ማክበርና ቀና ብሎ መራመድን እንጂ ለፍርሃት ማቀርቀርን አይደለም” ብለዋል።
ከአዘጋጆቹ አንዷ የሆነችው ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ “ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋዕትነት የታፈረች፣ የተከበረች በደም ዋጋ የተረከብናት
ናት” ስትል ተናግራለች።
“ለዘመናት የኖርንበትና የተጋመድንበትን የአንድነት መሰረት የሚገዳደርና ክብራችንን የሚገስ ተግባራትን አጥብቀን እንቃወማለን”
ብላለች።
መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያለ ሰቀቀን የሚኖሩበት ከተማና ገጠር መፍጠር፣ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር፣ ዳር ድንበር መጠበቅ
የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት መሆኑንም ገልጻለች።
በውስጥ ያሉ ልዩነቶች ሳይገድቡ ሀገር ለማኖርና ለማዝለቅ በአንድነት እንቆማለን፤ ዓባይን እያቀናን ያለነው የእናቶቻችንን ዓይን
በጢስ ከሚያጠፋ የማይገፋ ኑሮ ለመገላገል ነው ብላለች።
ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆንና በሕዝብ የሚመረጠው መንግሥት ከመላው ዓለም ጋር የሚኖረው
ግንኙነትና ውሳኔዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ የጸደቀ መሆን እንዳለበትም ተናግራለች።
የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ የሌላውን ሀገር መብት መንካትና መግፋት አለመሆኑን ኹሉም ሊረዳ እንደሚገባም ገልጻለች።
ኢትዮጵያዊያን ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ሰላም በየዘመናቱ ልጆቻቸውን የገበሩ መሆናቸውን በመረዳት ኹሉም ከኢትዮጵያ ጎን
እንዲቆም በንቅናቄው ጥሪ መቅረቡን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የንቅናቄ መርኃ ግብሩ በአደባባዮች፣ በጎዳናዎችና፣ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ተከናውኗል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየአማራ ልዩ ኃይል ሕዝብ ሊጠብቅ እንጂ ለወረራ አልመጣም፣ የልዩ ኃይሉ ተልዕኮ ሰላምን ማምጣትና ሕዝቡን መጠብቅ ነው” የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች
Next articleለኢንዱስትሪ ሽግግር ዩኒቨርሲቲዎች የንድፈ ሃሳብ ትምህርትን ከተግባር ጋር በማዋህድ መስጠት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡