
አንዳንድ የውጪ ሀገር መንግሥታት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ተደጋጋሚ ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ ተጠየቀ፡፡
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዩናይትድ ኪንግደም “ለኢትዮጵያ ዘብ እንቁም” ወይም “DEFEND ETHIOPIA”
ግብረኃይል በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ እንዲሁም በሀገር ቤት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር
በመተባበር በሀገር ቤት የሚገኙ የሲቪክ ድርጅቶች ላቀረቡት ጥሪ አጋርነትን ለመግለጽ “ብሔራዊ ክብር ፣ በሕብር” በሚል
በበይነ መረብ ተቃውሞውን አካሂዷል፡፡
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ያሉ አንዳንድ የምእራባዊያን ሀገሮች ከኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ዓመታት የቆየ ታሪካዊ
ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ያስታወሰው ግብረኃይሉ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ታሪካዊ ግንኙነቱን ሊያበላሹ
አይገባም ብለዋል፡፡
የውጭ ሀገራት በኢትዮጵያ የሚያከናውኗቸው መልካም ተግባራት እንዳሉ ግብረኃይሉ ጠቅስ በአሁኑ ጊዜ በውስጥ ጉዳይ ላይ
እያሳዩ ያለው ጣልቃ ገብነት ካላቸው ትብብር ያፈነገጠ ነው ብሏል፡፡
“የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት በሆነው የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት ለማንበርከክ የሚደረገው ጥረት ፈጽሞ
ተቀባይነት የሌለው ፣ የራሳችንን ችግር ለመፍታት አቅሙ ያለን እና ራሳችንን የምናውቅ በመሆኑ ከኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ
እጃቸውን እንዲያነሱ” ሲል ነው የጠየቀው፡፡
የኢትዮጵያን እድል ፈንታ የመወሰን መብቱ የዜጎች እንጂ የውጪ ሀገራት መንግሥታት እንዳልኾኑ በተቃውሞው ላይ የተሳተፉ
አካላት ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድብ ኹለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት መከናወኛ ጊዜ በመቃረቡ የሀገር ሰላም እንዲደፈርስ እና እርስ በርስ ለማጋጨት
የሚሠሩ ኃይሎችን ለመመከት ከምንጊዜውም በላይ በአንድነት ኢትዮጵያን መጠበቅ አለብን ብለዋል ተሳታፊዎቹ፡፡
በሕዝብ ምርጫ የሚሰየም መንግሥት እንጂ አንዳንድ ምእራባዊያን ሀገሮች እንዳሻቸው የሚጠመዝዙት እና ለራሳቸው ታዛዥ
በመሆን የሚሠራ የመንግሥት ሥርዓት ለማስቀመጥ የሚደረገውን ጥረት ፈጽሞ የማይቀበሉት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት መላው ኢትዮጵያዊ እንዲደግፍምጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዲፕሎማሲ ዘርፍ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሁሉም በውጭ ሀገር የሚገኝ ዜጋ በኢትዮጵያ ላይ ጣልቃ ለመግባት
የሚደረገውን ዘመቻ እንደ አባቶቹ ሁሉ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
“ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ” የሚለው ጣልቃ ገብነትን የሚቃወመው የኢትዮጵያዊያን ድምጽ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል
አስተባባሪው አቶ ዘላለም ተሰማ ገልጸዋል፡፡
የተቃውሞው ተሳታፊዎች የውጭ ሀገራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማክበር አለባቸው ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት
ከማከናወን የሚያግደን የለም ፣ ምርጫውን ማካሄድ የውስጥ ጉዳያችን ነው የሚሉና ሌሎች መልእክቶችን አስተላልፈዋል፡፡
በበየነ መረቡ ተቃውሞ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች እንደተካፈሉ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m