
ʺደፋር ሰው ከማዶ ቢሏቸው ደረሰ
የገነቡት ምሽግ በድንገት ፈረሰ”
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ተከዜን በድፍረት ከተሻገረበት እስከ ተከዜን በሀፍረት እስከተመለሰበት የነበረው ጉዞ፤ አማራ የሚል ስም የተሰጠው ጀግና ኢትዮጵያዊ ሕዝብ በተሰጠው ስም ብቻ የምድር የመከራ ገፈቶችን ሁሉ ቀምሷል፡፡ የጨለማ ማሰሪያዎች፣ የጅምላ መቃብሮች፣ የስቃይ ጥግ ማሳያ ማሰቃያዎች ሁሉ በአማራዎች ተሞልተው ኖረዋል፡፡ የሞላው ታሪኩን ሊያጎድሉ፣ ዘላለም ሕያው የሆነው ወኔውን ሊገድሉ፣ የተወደደው ስሙን ሊያስጠሉ፣ በጽኑ መሠረት ላይ የበቀለውን ታሪኩን ሊነቅሉ ያላደረጉት ያለ አይመስልም፡፡
ከእነ ነብሳቸው በገደል የተወረወሩ ነብሶች፣ ለመዳን የተማጸኑ አሳዛኝ ድምፆች ስጋቸውን አሳልፈው ያለጊዜያቸው ቢያልፉም ስሜታቸው አልጠፋም፡፡ የዋይታ ድምጻቸው ይሰማል፤ የድረሱልኝ ጥሪያቸው ይጣራል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ፣ የቃፍታ ሑመራ ተራሮች አፍ ቢያወጡ ስንቱ በተሰማ ነበር፡፡ ስንቱስ በሥራው ግፍ ባፈረ ነበር፡፡ እንደ ሰው ቢናገሩ፣ ያዩትን ሁሉ ቢመሰክሩ፣ የመዘገቡትን ሁሉ ቢዘክሩ ኖሮ ከሆነባቸው ይልቅ የሰሙት ምንኛ በተደነቁ ነበር፡፡ ያለ ጥፋት መክሰስ፣ ቀምቶ መሬትን ማረስ፣ ያለ በደል መውቀስ፣ ያለ ወንጀል ማስለቀስ፣ በሐዘን አንጀትን መበጣጠስ፣ ታሪክን ማርከስ ኹነኛ ተግባራቸው ነበር፡፡
ቀን ይጥላልም ያነሳልም፡፡ እንኳን በክፋት በበረከት የተመላ ምድራዊ ስልጣንም ዘላለማዊ ኀይል የለውም፡፡ መልካም ያደረገው ዘላለማዊ ስም ጥሎ ሊያልፍ ይችል ይሆናል፡፡ ዘላላማዊ ዙፋን ግን የለውም፡፡ የተቀበለውን ዙፋን አስረክቦ ማለፍ ግድ ይላልና፡፡ ከዋሻ እስከ ዋሻ በሚረዝመው የትህነግ ታሪክ ውስጥ ብዙ ነገሮች ታይተዋል፡፡ በዋሻ ተጀምሮ፣ በስልጣን ዳብሮ በዋሻ የተፈፀመው የትህነግ ዘመን ኢትዮጵያ ቀዳዳዎቿ እንዲበዙ አድርጓል፡፡ እሴት እንዲሸረሸር፣ ወንድም ወንድሙን እንዲጠረጥር፣ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ዘር እንዲከበር አድርጓልም፡፡
አንድ ተጓዥ መምህር በወልቃይት ጠገዴ፣ ቃፍታ ሑመራ ያዩትን በማስታዎሻቸው አስፍረውታል፡፡ መምህሩ በደረሱባቸው ሥፍራዎች የታዘቡትን ሚስጥር፣ የተመለከቱትን ሕይወት፣ ያገኙትን እውነት በጉዞ ማስታዎሻቸው መዝግበውታል፡፡ የጉዞ ማስታወሻቸውን ተመለከትኩት፡፡ ሊታወቁና ሊደረጉ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉበት ተሰማኝ፡፡ በጉዞ ማስታወሻቸው ከመዘገቡት እልፍ ሀሳብ ውስጥ ጥቂቶቹን ማክፈል ፈለኩ፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ጀምበሩ አረጋ ይባላሉ፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡ የትህነግ ክፉ በትር ወዳረፈባቸው አካባቢዎች ተጉዘው ሁሉን ተመልክተዋል፤ ታዝበዋል፡፡
ተጓዡ መምህር የጉዟቸው መጀመሪያ የሆነችውን የካቲት አሥራ አንድ 2013 ዓ.ምን እንዲህ ሲሉ ይገልጿታል፡፡ ʺየዛሬን አያድርገውና ሁሌም በየካቲት 11 ቀን ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በመንግሥት በጀት ያለማንም ከልካይ በመላ ሀገሪቱ በጭፈራ፣ በተጨማሪ ሴራ ጉንጎናና የማስፈራሪያ ድስኩር መጎሰሚያ ቀን ኾና ስትከበር እንደነበረ ገልጸዋል፡፡
የዚህ ዓመቷ የካቲት 11 ካለፉት 29 ዓመታት የካቲት 11ዶች የምትለይበት መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል ‘እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትፈርሳለች’ እያሉ ያለሰቀቀን የሚናገሩ ደፋሮች እንደ ጃርት ጉድጓድ ውስጥ ተወሽቀው ያሉበትና አንዳንዶቹ በውርደት የተማረኩበት፣ ስለትሕነግ ጀግንነትና ወደር የለሽነት ከትህነግ በላይ ትህነግ የሆኑ የአጨብጫቢ ሆድአደሮችን የመግላጫ ጋጋታ ያልሰማንበት ዕለት መኾኗ ነው” ብለዋታል፡፡
ተጓዡ መምህር መነሻቸውን ጎንደር አዘዞ አድርገው ከተከዜ መለስ ያሉትን የወልቃይት ጠገዴ፣ ቃፍታ ሑመራ አካባቢዎችን ቃኝተዋል፡፡ የካቲት 11ን እያስታወሱ የትህነግ የጉራ ተራራ በግፉዓን ቆራጥ ተጋድሎ እንደ እንቧይ ካብ ተንዶ ያ-ሁሉ የውሸት ክምርና ባዶ ፉከራ ውኃ በልቶት ሰማይ ተደፍቶባቸው በየስርቻውና በቀበሮ ጉድጓድ እየተሹለከለኩ ይገኛሉ ሲሉ መዝግበዋል፡፡ በሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይገመት ስቃይ በኢትዮጵያዊያን ላይ ለፈጸሙት ነውር መልስ ይሆን ዘንድ ምድራዊቷ ዓለም ፊቷን እንዳዞረችባቸውም አስፍረዋል፡፡ ለፈፀሙት በደል ካሳ ይሆን ዘንድ የምድርን ሲኦል የየዕለት ሕይወታቸው አድርገውታል፡፡
የትህነግ ርዝራዦች ጉድጓድ ውስጥ ተደብቀው የትግራይን ወጣቶች ወደ ሽምቅ ጦርነት እየከተቷቸው ስለ መኾናቸውና እነሱ ባመጡት መዘዝ ሰላማዊ የትግራይ ሕዝብም ለተለያዩ አደጋዎች መጋለጡንም አስፍረዋል፡፡ መንገደኛው በቅራቅር በነበራቸው ቆይታ ትህነግ የከለለችው ክልልና የሰጠችው ድንበር ሳያስገርማቸው አልቀረም፡፡
በሁለቱ ክልሎች መካከል የተሰመረው ወሰን የትምህርት ቤት አጥር ነበርና ነው፡፡ በራሷ ስልጣን የማይገባትን አካባቢ ከመውሰዷም አልፎ በወሰነችው ወሰን የትምህርት ቤት አጥር እንኳን ከወሰኗ ገባ ብሎ እንዳይተከል ትከለክል እንደነበር ጽፈዋል፡፡ የመከራዎቹ ዘመናት ሊያልቁ ሲቃረቡ፣ የትህነግም ዘመን ሊያከትም ሲጠጋ በአማራ ክልል ላይ ግልጽ ትንኮሳ ጀመረች፡፡ ይህም ትንኮሳ ምርጫ ባካሄደችበት ቀን ይጀመር ነበር፡፡ የአማራ ክልል የጸጥታ ኀይል ነገሩን በትዕግስት ተመለከተው እንጅ፡፡ ቀኑም አለፈ፡፡ ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም ደረሰ፡፡ የትህነግ ታጣቂዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፡፡ ለድል መነሻ ትሆን ዘንድ አብዝተው የሚመኟትን ቅራቅርን ለመያዝም ጥቃት ከፈቱ፡፡ በዚህ ጊዜ ያልተጠበቀ ጉዳይ ገጠማቸው፡፡ ድል እየሸተታቸው የመጡት የትህነግ አባላት ቅራቅር ናፈቀቻቸው፡፡ ድል ለተበዳዮች ኾነች፡፡ በተደጋጋሚ የሞከሩት ሙከራ መና ቀረ፡፡ ይባስ ብሎ የያዙትን ሥፍራ እየለቀቁ ነብሴ አውጭኝ ሸመጠጡ፡፡
ʺአላስቀምጥ ብለው ሲገፉት ሲገፉት
የአንበሶቹን መንጋ ቀስቅሰው አረፉት” እንዳለ ከያኒው የአንበሶች መንጋ ተነስቷልና፡፡ ማስተኛት የማይቻል ሆነ፡፡
መንገደኛው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ በአማርኛ ማውራት፣ በቋንቋቸው እየሰሙ በእውነት መዳኘት የናፈቃቸው የማክሰኞ ገበያ ነዋሪዎችን ችግር ቀርበው ተረድተዋል፡፡ ማንነቱን በመጠየቁ ብቻ ከእነነብሱ ገደል ውስጥ የተጣለን ታሪክ ተጓዡ ሲሰሙ ማዘናቸውን አስፍረዋል፡፡ ገደሉንም አይተውታል፡፡ የወልቃይት ደጀና እና የትህነግን ግንኙነት ያሰፈሩት መንገደኛው መምህር የደጀና ኮረብታማ ቦታዎች በውስጣቸው የወልቃይት ግፉዓንን ሚስጥር አሁንም ሸፍነው እንደያዙ ናቸው፡፡ በኮረብታዎቹ ስር መሬቱ ቢጫር የግፉዓንን የፈራረሰና በምስጥ የተበላ ቅሪተ-አጽም ማግኘት የተለመደ ነው በማለት አስፍረዋል፡፡
ትህነግ ቀደም ሲል የደጃና ኮረብታዎች የሰጡትን ጥቅም በማሰብ በሕግ ማስከበር ዘመቻውም ሥፍራውን ተገን አድርጎ ለመዋጋት ሞክሮ እንደነበር መንገደኛው ጽፈዋል፡፡ በደጀና የተሸነፈው ታጣቂም በአዲ ረመጥ (ወፍ አርግፍ) ሳለ ፋኖ መጣብህ በሚል ወሬ ብቻ አካባቢውን ለቆ መፈርጠጡን ከከተማዋ ሰዎች አገኘሁት ያሉትን እውነት አስፍረዋል፡፡
ʺደፋር ሰው ከማዶ ቢሏቸው ደረሰ
የገነቡት ምሽግ በድንገት ፈረሰ” እንዳለ ገና ዝናው ሲሰማ ምሽጋቸው ፈራረሰ፡፡ ወኔያቸውም ኮሰሰ፡፡
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ቀድማ በምትጠራው ወልቃይት ውስጥ ሺዎች ተፈናቅለዋል፣ ሺዎች ሞተዋል፣ ሺዎች ታስረዋል፤ ብዙዎች የደረሱበት ሳይታወቅ ቀርተዋል፡፡ መንገደኛው በወልቃይት ጠገዴ በአማርኛ መናገር፣ መዳኘት፣ የአማርኛ ዘፈን ማዳመጥ ትህነግን እንደመቃዎም እንደሚቆጠር ከነዋሪዎቹ ያገኙትን እውነት በማስታወሻቸው አስፍረው አስቀርተዋል፡፡
የተከዜን ወንዝ አካልሎ አምባ ብርኩታ ድረስ የሚያካልለው የመዘጋ ወልቃይት የእርሻ ሥፍራ ባለ ርስቶቹ የበይ ተመልካች ኾነው ዘመናትን እንደገፉ ተጓዡ መዝግበዋል፡፡ የመገፋት ዘመናቸው የተጠናቀቀላቸው የወልቃይት ነዋሪዎች ሕይዎትን በአዲስ መልክ እያጣጣሙት ነው፡፡ የወልቃይት ነዋሪዎች ሰው ተርበው እንደኖሩም መንገደኛው ጽፈዋል፡፡ ʺትህነግ የወልቃይትን ምድር ከረገጠበት ነሐሴ 1971 ዓ.ም ጀምሮ የወልቃይት ሕዝብ ሐብቱን፣ ልጆቹን፣ ደስታውን፣ ታሪኩን፣ ቋንቋውን፣ አጠቃላይ ማንነቱንና ሕይወቱን የተቀማ ሕዝብ ነው፡፡ ወገኔ ከሚለው የአማራ ሕዝብ ጋር እንዳይገናኝ በጥቁር መጋረጃ የተከለለ ሕዝብ ነበር፡፡ በስግብግቡ ቡድን የተገፋው ሕዝብ ወገኔ ከሚለውና በማንነቱ አንድ ከኾነው የአማራ ሕዝብ ጋር ከብዙ የመከራ ዓመታት በኋላ ሲገናኝ በስስትና በፍቅር መተያየቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ እውነትም የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ዓይኖች ወገን የተራቡ ነበሩ በማለት ከትበዋል፡፡
የሱር ኮንስትራክሽን በወልቃይት ጠገዴ ቃፍታ ሑመራ ሕዝብ ላይ ያደረሰውን ግፍና ከስሙ በስተጀርባ ሲሠራው የነበረውን ሸፍጥ መንገደኛው ጽሕፈዋል፡፡ የትህነግ ቡድን በሕይወት የእርሻ ሜካናይዜሽን ውስጥ የፈፀመውን አልጠግብ ባይነትም አስፍረዋል፡፡ በመልካሙ ምድር የሚገኘውን ሀብት ለመጠቀም አማራዎች ለመስዋዕትነት ቀርበዋል፡፡ ትህነግ በማይካድራ የፈፀመችው ግፍም በመንገደኛው ተከትቧል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ቀደም ሲል በዲቪዥን ስድስት መንደሮችን በመፍጠር ሠፈራ መመስረት እና በሌሎች አካባቢዎች ሠፈራን በማበራከት የነበራትን ተስፋፊነትም በማስታወሻቸው አመላክተዋል፡፡ የሰፈራው ዓላማም አማራን ማፈናቀልና አካባቢውን በአጭር ጊዜ ለመለወጥ ካላቸው አደገኛ የመስፋፋት እቅድ ነበር፡፡ አካባቢው የአማራ ክልል ብለው ለከለሉት ቅርብ ስለኾነና በአንድ ወቅት የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ያነሳል የሚል ስጋት ስለነበራቸው ጥያቄው ከመግፋቱ በፊት አካባቢውን የራሳቸው ማድረግና አስቀድሞ በር መዝጋት ነበር ዓላማቸው ብለዋል፡፡ በዚህ አህጉር አቋራጭ መንገድ የሚያልፍ አላፊ አግዳሚን አካባቢው ፍጹም የራሳቸው ሕዝብ ብቻ እንደሚኖርበት በቀላሉ ለማሳመንና በዚህ አካባቢ ሌላ ሕዝብ የለም፣ አልነበረምም የሚል የፖለቲካ ሥራ ለመሠራት ታቅዶ የተከናወነ አደገኛ የትህነግ ሴራ ውጤት መኾኑንም መንገደኛው ጽሕፈዋል፡፡ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ስግብግብ ፍላጎቶቹን ለማሳካት አማራዎችን በማጥፋትና በማፈናቀል በራሱ ቋንቋና ባህል እንዲቀየር መሥራታቸውን ተመልክቻለሁም ብለዋል፡፡
በዚህም እንደመሳሪያነት የተጠቀሙበት ሰፈራ በስፋት ማካሄድ፣ የአማራን ሕዝብ ማፈናቀልና ማጥፋት፣ ትግርኛ ቋንቋ ብቻ የአካባቢው መግባቢያ እንዲሆን በሕዝቡ ላይ ግዳጅ መጣል፣ ቀደምት የነበሩ የቦታ ስያሜዎችን እያጠፉ በአዲስ በራሳቸው ቋንቋ ስያሜዎች መተካት፣ የሕጻን ልጅ ስም አወጣጥ ሳይቀር በቋንቋቸው እንዲሆን ማድረግ፣ የአማራ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ የሚኖርባቸውን ቦታዎች እንዲዳከሙ በማድረግ ሌሎች በራሳቸው ቋንቋ ስያሜ ያላቸው አዳዲስ ከተሞችን በመመሰረት የሕዝቡን ታሪክ ማጥፋት፣ የንግድ ቤቶችና ድርጅቶች የትግርኛ ስም ብቻ እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ የአማራን ሕዝብ ወግ፣ ባሕል፣ ታሪክና ትውፊት ያውቃሉ የተባሉ አባቶችንና ሽማግሌዎችን ማጥፋትና ሌሎችንም ግፎች መፈጸማቸውን ከትበዋል፡፡
ትህነግ አማራን የማዳከምና የመስፋፋት ዕቅዷን ያወጣችው በጫካ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
ከዓመታት መራር ትግል በኋላ በግፍ የሄደው ማንነት መመለሱን የሚጠቅሱት መንገደኛው በዚያ አካባቢ ቢደረጉ የሚሏቸውንም ከጉብኝታቸው በኋላ አመላክተዋል፡፡ በነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ የራሱን ሰላም እንዲያስጠብቅ ማደራጀት፣ ማሰልጠን፣ ማሰማራትና ተገቢውን ሁለንተናዊ ድጋፍና ክትትል ማድረግ፤ በየወቅቱ እየገመገሙ ማስተካከያ ማድረግ፤ በድንበር አካባቢ በሚገኙ ከተሞች ጥቃት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ፤ በትህነግ ግፍ ምክንያት የስደት ኑሮ እየገፉ ያሉ ግፉዓንን ወደቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ፣ በአካባቢው ስለተፈጸሙት የዘር ማጥፋት ወንጀሎችና ተያያዥ ድርጊቶች የተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን እና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን በመጠቀም የወንጀሉን ስፋትና ጥልቀት ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በትህነግ ተይዘው የነበሩ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች በተለይም ሕይወት እርሻና መዘጋ ወልቃይት ጦም እንዳያድሩ ማምረት እንዲችሉ ማድረግ፣ የተፈጸሙ የዘር ፍጅቶችንና ዘረፋዎችን መሰነድና ለግፉዓን የሞራል፣ የሕይወትና የንብረት ዘረፋ ካሳዎችን እንዲከፈል የሚያስችል ማስረጃ ማሰባሰብና የሕግ ነክ ጉዳዮችን የሚሠራ የባለሙያዎች ቡድን አደራጅቶ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የትህነግ አሸባሪ ቡድን በማይካድራ ነዋሪዎች ላይ የፈጸመው ግፍ ለወደፊቱ በየትኛውም የሀገሪቱ ሕዝብ ላይ እንዳይደገምና ማስተማሪያም ይኾን ዘንድ የሰማዕታቱን መታሰቢያ ማቆም ይገባል ነው ያሉት፡፡
እንደ ሀገር ስለልዩነት የምናወራበት ሳይኾን ሀገር ስለማስቀጠል የጋራ አቋም መያዝ ይገባናልም ብለዋል፡፡ ተጓዡ መምህር ለአራት ቀን በቆዬው ጉብኝታቸው ብዙ ጉዳዮችን አይተዋል፤ ሰምተዋል፣ በማስታወሻቸውም አስፍረዋል፡፡ እኛም በጥቂቱ ገለጽነው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ