
የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚካሄደውን የውጭ ጣልቃ ገብነት አወገዘ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13 ቀን 2013 (አሚኮ) መሠረቱን በአሜሪካ ያደረገው የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚካሄደውን የውጭ ጣልቃ ገብነት አወገዘ።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ ወይም አንድ ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት በውጤቱ ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር የሚሞክሩ ኹሉም የውጭ ኃይሎችን እንደሚያወግዝ ነው ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በላከው ደብዳቤ የገለጸው።
ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት የዴሞክራሲ ምሰሶዎች አንዱ የሆነውን ግልጽ ምርጫ ለማካሄድ ገለልተኛ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ማቋቋሟን አውስቷል። ይህም ለዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ሽግግር አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን ነው ያመለከተው።
“የምርጫ ሂደት ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ ወይም አንድ ድምፅ ከመስጠቱ በፊት በውጤቱ ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር የሚሞክሩ ኹሉንም የውጭ ኃይሎችን አጥብቀን እናወግዛለን” ብሏል።
“የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ ጉዳዮች የሰጠውን ትኩረት እያደነቅን በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ላይ አላስፈላጊ የሆነ ጣልቃ ገብነት ግን የሚያስከተለው አደጋ ያሳስበናል” ያለው ምክር ቤቱ፤ በኢትዮጵያ የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ እንደሆነ አስገንዝቧል።
የትኛውም ሉዓላዊ ሀገር እንዲህ አይነት ክህደት ሲፈጸምበት ሊወስደው የሚችለውን እርምጃ የኢትዮጵያ መንግሥት መውሰዱን በማመልከት፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ሊደገፍ ይገባል” ብሏል።
“ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከኢትዮጵያ ጋር የምትሠራው አሜሪካ ኢትዮጵያንና ቀጣናውን ለማተራመስ የሚሠራውን የሕወሓት የሽብር ቡድን ደጋፊዎችና የውጭ ተባባሪ ድርጅቶችን መከታተል ይኖርባታል” ሲል አስገንዝቧል።
“አሜሪካ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ፣ ለሁለተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ድጋፍ እንደምትሰጥና በኢትዮ-ሱዳን መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ በውይይት እንዲፈታ እንዲሁም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚካሄደው የመልሶ ግንባታና የሰብዓዊ ድጋፍን በማገዝ አሜሪካ ገንቢ ሚና እንደምትጫወት እምነታችን ነው” ብሏል።
ምክር ቤቱ “ከ115 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውና በፕሬዚዳንት ቴዲ ሩዝቬልት የመሪነት ዘመን የተጀመረው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ጠንካራ ወዳጅነት እና የረጅም ጊዜ አጋርነት በጋራ ብልጽግና ወደፊት እንደሚራመድ እናምናለንም” ሲል መግለጹን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ