
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ሆኖ መካሄድ በሚችልበት ጉዳይ ላይ ከአጋር አካላት ጋር እየመከረ ነው።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሀገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ ያሉ ሂደቶች ዲሞክራሲያዊ መርህን ተከትለው መከናወን ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ነው ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ የሚገኘው።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ሀገራዊ ምርጫው ኢትዮጵያ የገጠማትን ውስጣዊ ችግር የምትሻገርበትና እየገጠማት ያለውን ውጫዊ ጫና ተቋቁማ ዲሞክራሲን እውን የምታደርግበት በመሆኑ ትልቅ ትርጉም እንዳለው አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩት ምርጫዎች የአገዛዙን ፍላጎት ለማሟላት የተካሄዱ እንደነበር ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል፡፡ በቅርቡ የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ተቀባይነት ያለው እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የብዙኀን መገናኛ ድርጅቶች፣ መንግሥት፣ ፓርቲዎችና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ኹሉ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ ማኅበረሰቡን እያጋጠሙት ያሉና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለይተው መሥራታቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው።
ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደትን በመከተል በምርጫ ወቅትም ይሁን ከምርጫ በኋላ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ቀድመው በመቀነስ ሀገር የማዳን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በምርጫው ሂደት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ ቅቡልነት እንዲኖረው የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የውይይት መድረኩ በዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምሕርት ክፍል የተዘጋጀ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የሲቪክ ማኅበራት አባላት፣ ምሁራንና ተማሪዎች ተሳታፊዎች ናቸው።
ዘጋቢ፡-ኃይሉ ማሞ-ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ