
“የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ውሳኔን የተላለፈና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጥስ ነው ” የአማራ ማኅበር በአሜሪካ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ማኅበር በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ በመቃወም ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጫ የወልቃይትን ወይም እርሳቸው እንደሚሉት “ምዕራባዊ ትግራይ” አካባቢን ጥንታዊ የፖለቲካ አስተዳደር መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ተፈፀመ የሚሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሜሪካን ካሳሰባት በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረውን የዘር ማጥፋት እርምጃ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባ ነበር ብሏል ማኅበሩ በምላሹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በተደጋጋሚ የአማራ ልዩ ኃይል እና የወልቃይት አማራዎችን ጉዳይ በሚመለከት የሚሰጡት መግለጫ ማኅበሩን ቅሬታ እንዳሳደረበት ጠቅሷል፡፡
የወልቃይት እና አካባቢው ሕዝብ አሁን ላይ እየተመራ ያለው ሕዝቡ በመረጣቸው የአካባቢው ተወላጆች መሆኑን የጠቀሰው ማኅበሩ የወልቃይት አማራ ሕዝብ በአሸባሪው ሕወሃት የአገዛዝ ዘመን ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ወደ ትግራይ እንዲጠቃለል የተፈፀመበትን ግፍ፣ መከራ እና ግድያ ሚኒስትሩ ችላ ብለውታል ወይም ለማሳታወስ ፈቃደኛ አይደሉም ነው ያለው የማኅበሩ መግለጫ፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የአማራ ማኅበር በአሜሪካ መጋቢት 2/2021 (እ.አ.አ) ያወጣውን ዝርዝር መግለጫ መመልከት በቂ ማስረጃ ነበር ብሏል፡፡ በአሸባሪው ሕወሃት አገዛዝ ወቅት ከአማራ በኀይል ወሰዷቸው በነበሩ ወልቃይት ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምት፣ ራያና አላማጣ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አሜሪካ የማጣራትም ሆነ የመመርመር ፍላጎት አልነበራትም ሲልም መግለጫው ይወቅሳል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን መግለጫ አሜሪካ ሕወሃት ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያዊያን በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ ስታደርሰው የነበረውን ዘረኛ አገዛዝ የምትደግፍ አስመስሏታል ነው ያለው፡፡ የአንቶኒ ብሊንከን መግለጫ ከመሰረቱ ስህተት መሆኑ ቢታወቅም ኢትዮጵያን እና ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ታሪክ በደንብ ለማያውቁ የዓለም ሀገራት እና ሕዝቦች የተዛባ አስተሳሰብን የሚያስይዝ ነው ይላል፡፡
መግለጫው በቅርቡ ሕወሃት ባስታጠቀቻቸው እና ባሰማራቻቸው ወጣት ገዳዮች አማካኝነት በማይካድራ የተጨፈጨፉትን አማራዎች በደል ከግምት ያስገባ አይደለም ብሏል የማኅበሩ መግለጫ፡፡
ማኅበሩ አሜሪካ ትግራይ ክልልን በተመለከተ እያራመደችው ያለው አቋም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጥስ ነው ብሏል፡፡
የአሜሪካ አካሄድ እና የብሊንከን መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀፅ 7 እና የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አንቀጽ 39 ውሳኔን የተላለፈ እና የሚፃረር ጣልቃ ገብነት ነው ብሏል ማኅበሩ፡፡
አሜሪካ በኢትዮጵያ እና በአማራ ሕዝብ ላይ የምታራምደውን ተገቢ ያልሆነ አካሄድ በመቃወም ማኅበሩ በተደጋጋሚ ቅሬታ ቢያቀርብም በቸልታ ታልፏል ይላል፡፡
የማኅበሩ መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከተፈፀሙ ሕግ ማስከበር ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት እና የሚያሰማራው የጸጥታ መዋቅር ኾኖ ሳለ የአማራ ልዩ ኃይል አካባቢውን ለቆ ይውጣ በሚል የወጣው የአሜሪካ መግለጫ ችግሩን ለይቶ ካለማወቅ እና የአማራ ልዩ ኃይልን ከኢትዮጵያ ውጭ ያለ ኃይል አድርጎ እንደመመልከት ይቆጠራል ብሏል፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አሜሪካን የሚያሳስቧት ከሆኑም በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጉራ ፈርዳ እና ማይካድራ አካባቢዎች የተጨፈጨፉ አማራዎችን በዘር ማጥፋት እርምጃ አብሮ በዓለም አቀፍ ገለልተኛ አጣሪ አካል ሊመረመር እንደሚገባ መግለጽ ይጠበቅባት ነበር ነው ያለው፡፡
“አሜሪካ በአማራዎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እውቅና መስጠት አትፈልግም” ያለው የማኅበሩ መግለጫ ስለሆነም ካለፈው ክረምት ጀምሮ ማይካድራን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በአማራዎች ላይ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እውቅና እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በቀጣይም ማኅበሩ ከብሊንከን ጀምሮ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ እንደሚወያይም በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ