
ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ኀላፊነት ወስደው እንደሚሠሩ የመተከል ዞን የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተናገሩ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በመተከል ዞን በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በተከሰተው የሰላም እጦት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ንጹሃን ተገድለዋል፣ በርካታ ሀብትና ንብረት ወድሟል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መኖሪያ ቀያቸውን ለቅቀው ተፈናቅለዋል።
የዞኑ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እኩይ ድርጊቱ የሚያሳፍር ቢሆንም ለዘመናት የቆየውን ሕዝባዊ አንድነት፣ መተሳሰብና አብሮነት እንዲሸረሽር መፍቀድ አይገባም ብለዋል። ይልቁንም ይበልጥ ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር መመከት እንደሚገባ ነው የሥራ ኀላፊዎቹ የተናገሩት።
የዳንጉር ወረዳ አስተዳዳሪ ብርሃኑ ክንፉ በመተከል ዞን በተከሰተው ሞት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል ከልብ አዝነናል ብለዋል። በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት “በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ‘ጽንፈኛ’ ኀይል በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሩ የማይነጣጠል ሕዝብን ገድሏል፣ አፈናቅሏል፣ በርካታ ሀብትና ንብረት ዘርፏል ነው ያሉት።
ዜጎች በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዲወድቁም ምክንያት ሆኗል። ሰላማዊ የጉሙዝ ተወላጆች በፍርሃት ወደ በርሃ ገብተው በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ፣ ሕጻናት በርሃብ ጅራፍ እየተገረፉ ነው፣ እናቶች ምቹ ሁኔታ በሌለበት ጫካ ውስጥ አምጠው እንዲወልዱ ተገደዋል፣ አለፍ ሲልም ለሕልፈተ ሕይወት ተጋልጠዋል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።
በተመሳሳይ ከሰሞኑ የጣለውን ዝናብ ተከትሎ ቻግኒ በሚገኘው የራንች ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ በተጠለሉ ተፈናቃዮች ላይ ደራሽ ጎርፍ በመከሰቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል። ሁኔታው ሳይጠነክር ቀድሞ ተፈናቃዮችን ለመመለስ ዝግጁ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
የማንዱራ ወረዳ አስተዳዳሪ ቢመር አምሳያ ደግሞ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚጥሩት የሥልጣን ፍላጎት ያላቸው ኀይሎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፣ ሕዝቡ ግን በሰላም ወጥቶ መግባት የሚሻ፣ በጥረቱ ሀብትና ንብረት አፍርቶ የሚኖርና ለመንግሥት ግብር የሚከፍል መኾኑን ተናግረዋል።
መተከል ዞን በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች ከፍተኛ ምርት የሚገኝበት እንደኾነ ይታወቃል ነው ያሉት። የደረሰው የሰላም እጦት መንግሥትን የተፈታተነ እና ሕዝብን ያሰቃየ መኾኑን ጠቅሰዋል። “ዓላማችን ተፈናቃዮችን መመለስና ማቋቋም ነው” ያሉት አቶ ቢመር ለዚህም ተቀራርቦ መወያየት ወሳኝ እንደኾነ አስገንዝበዋል። “የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋምም ኀላፊነት እወስዳለሁ” ብለዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ጋሹ ዱጋዝ እንዳሉት ክረምት ከመግባቱ በፊት ተፈናቃዮች በልዩ ሁኔታ ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱና እንዲቋቋሙ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ ዕቅድ ተዘጋጅቷል። ከተመለሱ በኋላም መንግሥት ልዩ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። ሸፍተው የነበሩ ኀይሎች መንግሥት ያደረገላቸውን የሰላም ጥሪ መቀበላቸውም በአካባቢው ያለውን አንጻራዊ ሰላም ያጠናክራል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ