
የዲከረንስ ችግኝ በመትከል ተጠቃሚ መሆናቸውን በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የፋግታ ለኮማ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች ችግኞች እየተተከሉ ይገኛሉ፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ እንድታገኝ፣ ለአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ግንባታና ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውኃ መጠን መጨመር ያገዛል፡፡ በዘንድሮው የክረምት ወራት በሀገረ አቀፍ ደረጃ የሚተከል 7 ቢሊዮን ችግኝ እንደተዘጋጀም ይፋ ተደርጓል፡፡
አማራ ክልል ደግሞ በ182 ሺህ 976 ሄክታር መሬት ላይ 1 ነጥብ 83 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል መዘጋጀቱን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል፡፡ በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች 38 በመቶ የደን ሽፋን ያለው የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደርም 105 ሚሊዮን ችግኝ ለተከላ ማዘጋጀቱን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም በብዛት የዲከረንስ ችግኝ ከሚተከልባቸው አካባቢዎች መካከል የብሔረሰብ አስተዳደሩን ፋግታ ለኮማ ወረዳ ቅኝት አድርጓል፡፡ አርሶ አደር ዓይናለም ታረቀኝ በፋግታ ለኮማ ወረዳ አሸዋ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከስድስት ዓመታት በፊት ጀምረው የዲከረንስ ችግኝ በመትከል ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያገኙ ነው፡፡
በሚያገኙት ጥቅም በመነሳሳትም በየዓመቱ 2 ሺህ 500 ካሬ ሜትር መሬት የዲከረንስ ችግኝ እንደሚተክሉ ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮም የተለመደውን ተግባር ለማከናወን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡ ከስድስት ዓመታት በፊት የተከሉትን የዲከረንስ ዛፍ ዘንድሮ በ44 ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ ዲከረንስ ማልማት ከመጀመራቸው በፊት ልጆችን በአግባቡ ለማስተማርና የቤት ወጪ ለመሸፈን ሲቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አረንጓዴ ልማቱ ግን ችግር ፈቺ እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡
የዲከረንስ ችግኝ ተተክሎበት የነበረውን መሬት ከተክሉ በሚራገፈው ቅጠል የአፈር ለምነቱ እንዲሻሻል እየተደረገ ነው ብለዋል አርሶ አደር ዓይናለም፡፡ በመኾኑም “የመሬት ዶክተር” ሲሉ ዲከረንስ ግራርን ገልጸውታል፡፡
ሌላው አርሶ አደር በላይነህ አድማሱ ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት የዲከረንስ ችግኝ በመትከል ላይ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደነገሩን በደን ልማት ሥራ መሰማራታቸው በርካታ ጥቅሞችን እንዲያገኙ አግዟቸዋል፡፡ ችግኝ ከተከሉት መሬት ውስጥ ለሁለትና ሦስት ዓመታት በቆሎ፣ ድንችና ሌሎችን ሰብሎችም በመዝራት እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል፡፡
ችግኙ ሲደርስ ቆርጠው ከሰል በማክሰል ደግሞ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ አስችሏቸዋል፡፡ ችግኙ ተቆርጦ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ደግሞ የመሬቱ ለምነት የበለጠ ተሻሽሎ ማገኘታቸውን አስረድተዋል፡፡ የችግኝ ልማቱ ገቢያቸውን በማሳደግም ኑሮአቸው እንዲሻሻል አድርጎታል፡፡
የፋግታ ለኮማ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ አበባው በለው በወረዳው ለአረንጓዴ ልማት ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከወረዳው ከአጠቃላይ የቆዳ ሽፋን ከ51 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዲከረንስ ግራር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡ የዲከረንስ ግራር በቀላሉ የሚበቅል፣ ቶሎ የሚደርስ እና ከተቆረጠ በኋላ የመሬቱን ለምነት በማሻሻል የሰብል ልማቱን ምርት ከፍ በማድረግ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ስለሚያደርግ አርሶ አደሮች በስፋት በዘረፉ እየተሳተፉ ነው ብለዋል፡፡
በወረዳው በብዛት እየተተከለ የሚገኘው የዲከረንስ ግራር ከአራት ዓመታት በኋላ ጥቅም ላይ ይውላል ያሉት ኀላፊው ለከሰል፣ ለማገዶ፣ ለአጥርና ለቤት መሥሪያ እንደሚያገለግልም አስረድተዋል፡፡ ዘርፉ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በወረዳው በየዓመቱ እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ ልማት ሥራ ብዙ ሰንሰለቶች እንዳሉት አቶ አበባው አስረድተዋል፡፡ ችግኝ በማፍላት፣ በመትከል፣ በመቁረጥ፣ ከሰል የሚይዝ ኬሻ በማዘጋጀት፣ በጫኝና አውራጅ ለተሰማሩትና መኪና የሚያቀርቡ ባለሃብቶችን ተጠቃሚ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡
አረንጓዴ ልማት ሥራው የመሬት ለምነቱን በመጨመር የአርሶ አደሮችን የማዳበሪያ ወጪ እየቀነሰ ነውም ብለዋል፡፡ ፋግታና አካባቢው መሬቱ ተሸርሽሮ ለምነቱን በማጣቱ የአፈር አሲዳማነት በስፋት የሚከሰትበት በመሆኑ ለሰብል ምርት ምቹ እንዳልነበር ምክትል ኀላፊው ጠቅሰዋል፡፡ አረንጓዴ ልማት ሥራው ይህንን ችግር በመቅረፍ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፤ አርሶ አደሮችም ጥቅሙን በመረዳት በስፋት እየተሳተፉበት ነው ብለዋል፡፡ ኀላፊው ወረዳውም ከከሰል ታክስ በዚህ ዓመት ብቻ 47 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል፤ የአርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናም ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የግብርና መምሪያ ኀላፊ የትዋለ ጌታነህ ብሔረሰብ አስተዳደሩ ከአጠቃላይ የቆዳ ስፋት ከ38 በመቶ በላይ የደን ሽፋን ያለው አካባቢ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ በየዓመቱ ከሚተከለው ደን 13 በመቶ የሚኾነው ሰው ሠራሽ ነው ያሉት ኀላፊው 8 በመቶ ደግሞ የዲከረንስ ችግኝ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በብሔረሰብ አስተዳደሩ በየዓመቱ በሚተከለው ችግኝ አንድ በመቶ የደን ሽፋኑን እየጨመረ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ዓመትም 105 ሚሊዮን ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡ ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስም 72 ሚሊዮን ችግኝ ቆጠራ ተደርጓል፡፡ አርሶ አደሮችም የገጠር መሬት አጠቃቀም ሕግን መሰረት በማድረግ እንደየአካባቢው የአየር ሁኔታ የአረንጓዴ ልማት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ መምሪያው እየሠራ መኾኑን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ