“…ለወራት ያጣጣምነውን ነፃነት ለዓመታት ማጣጣም ስለምንሻ የአማራ ልዩ ኀይልንና ሚሊሻ አይንኩብን”የአካባቢው ነዋሪዎች

249
“…ለወራት ያጣጣምነውን ነፃነት ለዓመታት ማጣጣም ስለምንሻ የአማራ ልዩ ኀይልንና ሚሊሻ አይንኩብን”የአካባቢው ነዋሪዎች
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) 40 ዓመታት ሲገደሉ ዝም ያለ፣ ነፃ ሲሆኑ አለሁ አለ። ምድርና ምድራዊያን ለተበዳዮች ፊታቸውን ያዞሩ ይመስላሉ። ፍርድ ምላስና ሀብት ወዳላቸው አዙራለች። ፍትሕ ሚዛኗን አጋድላለች። በሟች ለቅሶ ለገዳይ ይለቀስ ተጀምሯል። ከተበዳዩ ድምፅ አስቀድሞ የበዳዩ ድምፅ ይሰማል። ፍርድ ሲያጋድል፣ ደሃ ሲበደል ዓለም አካሄዷ ይጠፋታል።
ዜጎች ማደሪያቸው በጨለማ ሲሆን፣ በግፍ ሲገደሉ፣ ሳይሞቱ ሲቀበሩ፣ ዘር እንዳይኖራቸው ሲሰለቡ የሰማ ጆሮ፣ ያየ ዓይን፣ ተው ያለ አንደበት አልነበረም። ይልቁንስ በዚያ ምድር ሰላም አለ፣ ልማት ደርቷል፣ ገበያው ሞልቷል፣ ዲሞክራሲ ተዘርግቷል ይባል ነበር።
“ዳኛውም ዝንጀሮ መፋረጃው ገደል፣ የት ላይ ተሁኖ ነው የሚነገር በደል” እንዳለ ከያኒው አሳሪዎቹም፣ ተናጋሪዎቹም፣ ፈራጆቹም፣ ከሳሾቹም አንድ አይነት ስለነበሩ የወልቃይትን ድምፅ የሰማው አልነበረም። ስለ ወልቃይት ሰቆቃ ድምፁን ያሰማ ሀገር፣ ተቋም፣ አልነበረም። የተበደለውም ሕዝብ ስለ ነፃነት ታገለ፣ ስለ ማንነቱ ተውኝ አለ። ያን ጊዜ የደበዘዘችው ጀንበር ፈገገች፣ ያጋደለችው ሚዛን ተስተካከለች፣ የጨለመችው የሰቆቃ ምድር ብርሃን ለበሰች። ነፃነት የተነፈጋት ቀዬ ነፃ ሆነች። ቀሚስ ሲመረጥላት የነበረች እናት መርጣ ለበሰች። በደስታ አጌጠች።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ የአማራ ሕዝብ ለቀናት አይደለም፣ ለሳምንታትም አይደለም፣ ለወራትም አይደለም ለዓመታት የግፍ ጽዋ ተጎንጭቷል። እንዳይናገሩ ተከልክለው አንደበታቸውን ዘግተዋል። ነፃነታቸውን ተወርሰዋል። ማንነታቸውን ተቀምተው በወንጀለኞች ፍርድ ቤት ችሎት ውለዋል። ዳሩ የሚፈርድ ዳኛ አልነበረም እንጂ። ስለ ነፃነት ፍትሕ የት ነሽ ያላሉበት ቀን አልነበረም። የተወሰደውን ማንነት፣ የተዘረፈውን ነፃነት ለመመለስ እየሞቱ እየታሠሩና እየተፈቱ ታግለዋል። አንደኛው ሲሞት ሌላኛው እያስቀጠለው ትግላቸውን አላቋረጡም ነበር። ሲሞቱ እየበዙ፣ ሲገፉ እየተነሱ ተጓዙ እንጂ።
እስራኤላውያን በግዞት የነበሩት ከሀገራቸው ወጥተው ነው። የወልቃት ሰዎች ግን በግዞት የኖሩት በሀገራቸው ነው። በሀገሩ በግዞት መኖር ምን ያክል እንደሚከብድ የሚያውቀው ተበዳዩ ብቻ ነው። በአሻገር ላለው ቀላል ሊመስለው ይችላል። ዘመን ዘመንን ተክቶ፣ በግፍ የፈሰሰው የንጹሃን ደም ፍሬ አፍርቶ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ነዋሪዎች ነፃነታቸውን መለሱ። የማንነታቸውን ካባ አሳምረው ለበሱ። እነርሱ ነፃ ሲሆኑ ኀያላን ነን ባይ ሀገራት ተከፉ።
በወልቃይት ለቅሶ ከሚገኘው ትርፍ የሚቀምሱ ሁሉ ደነፉ። በሰቆቃው ዘመን ያልተመለከተው ዓይናቸው፣ ያልሰማው ጀሯቸው፣ ያልተናገረው አንደበታቸው ተከፈተ። ስለ ወልቃይት ሊናገሩ፣ ስለ ማንነት ሊመሰክሩ፣ ስለ ነፃነት ሊመክሩና ሊዘክሩ ከጀላቸው። ለካስ በወልቃይት ለቅሶ ሰርግ ይሰረግ ኖሯል። ልጅ ይድሩ ይኩሉ ኖረዋል። ወልቃይት ሲደሰትና የራሱን ሰርግ ሲያሰርግ በእነርሱ ቤት ለቅሶ ሆነ። የወልቃይት የተወሰደ ማንነት ከተመለሰ ወዲህ ከተራ ጥቅመኛ እስከ ታላላቅ ፖለቲከኛና ሀገራት ድረስ ሀሳባቸውን ሲሰጡ ይታያሉ። በወልቃይት ጉዳይ እጃቸውን ሊያስረዝሙ የሚከጅሉም አልታጡም።
የአሸባሪው የትህነግ ትርፍራፊዎችም የወልቃይትን ማንነት ዳግም እንገፋለን እያሉ ሲጋጋጡ ይስተዋላሉ። ዘመኑ ያለቀባቸው እንደኾነ ግን አልተገነዘቡም። የአካባቢው ነዋሪዎች ለነፃነታቸው ከከፈሉት ዋጋ ባልተናነሰ በነፃነታቸው ላይ የሚቆምረው ያበሳጫቸዋል። የአካባቢው ተወላጅና ነዋሪ ካሳ ጥሩነህ “አሸባሪው ትህነግ በ1972 ዓ.ም ሲመጣ እየገደለን ገባ። በ2013 ዓ.ም እየገደለን ወጣ። ከእኔ ማኅደር ብቻ 116 በግፍ የተገደሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ጀግኖች፣ ሀብታሞች፣ ተሰሚነት ያላቸውና ታሪክ አዋቂዎች ስለሆኑ ነው የተገደሉት። ትህነግ ማለት ገዳይ ነው። ብዙዎች ዘር እንዳይኖራቸው ተኮላሽተዋል” ነው ያሉን።
ወያኔ በትግል አካባቢውን ለቆ ከወጣ በኋላ ነፃነት መጥቷል፣ በግፍ መገደል፣ መታሰርና መንገላታት ቀርቷልም ብለውናል። ለዚህም ልዩ ኀይሉ ሚሊሻውና መከላከያው የከፈለው መስዋትነት ግሩም ነው።
የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ሕይወቱን ሰጥቶ ሰላም ያመጣና ረፍት ሳይኖረው ሀገር እየጠበቀ ያለ ነው። የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ባይኖር ኖሮ እስካሁን ድረስ የመኖራችን ነገር አጠያያቂ ነበርም ነው ያሉት። ልዩ ኀይሉ ባይኖር የጀመሩትን ግፍ በእኛ ላይ ይጨርሱት ነበርም ብለውናል። ፀረ ሕዝቦች የራሳቸውን ጥቅም ነው የሚያዳምጡት። ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ስንታገል ነው የኖርነው፣ በነዚህ ሁሉ ዓመታት ግን እንዴት ሆናችሁ? ብሎ የጠየቀን አልነበረም።
አሁን ግን ነፃነታችንን ስናገኝ በነፃነታችን የሚቀልዱ ሀገራትና ተቋማት መጥተዋል ነው ያሉት። “እኔ ስለ አንተ እናገርልሃለሁ የሚለንን አንፈቅድለትም። በማንነታችን ማንም ሊመጣብን አይገባም። የተቀማነውን ማንነት አግኝተናል፣ ይህንንም ያለማንም ይሁንታ እናስቀጥላለን። በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጣልቃ የሚገቡ ሀገራት ይታቀቡልን፣ እኛ እስካሁን የደረሰብን ግፍ ይበቃናል” ብለዋል፡፡
መምህር ሠለሞን አቡሃይም ያን ጊዜ ሲያስታውሱ “አንገታችን ደፍተን፣ አንደበታችን ዘግተን በመስማት ብቻ ነው የኖርነው፣ እንድንናገር የሚፈቅድልን አልነበረም” ነው ያሉት። ወያኔ በሚያራምደው መስመር የሄደ፣ ሁለተኛ ዜጋ ቢሆንም ከሞት ይድናል። የእነርሱን መንገድ የተቃወመ ግን መኖር እንደማይችልም ተናግረዋል። “የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አሁን ላይ ነፃነቱን እየተናገረው ሳይሆን እየኖረው ነው፣ አሁን ሙሉ ነፃነት አለን። የተወሰደብን ማንነት ተመልሷል” ብለውናል።
ትናንት አያሌ መከራዎች ቢደርሱባቸውም ዛሬያቸውን እያዩ ወደ ደስታቸው ማድላታቸውንም ነግረውናል። “በቋንቋችን እየተናገርን፣ በባሕላችን እየተዋብን፣ በሚመስለን እየጨፈርን ነውም” ነው ያሉት። “የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ይውጣ ማለት በህይወት የተረፈውን ሕዝብ ዳግም ለማስጨረስ ነው። ለወራት ያጣጣምነውን ነፃነት ለዓመታት ማጣጣም ስለምንሻ ዘባችንን አይንኩት” ብለውናል።
ልዩ ኀይሉ ከወጣ ለማን ሊሰጡን ነው? ሀገሩንስ ማን ሊጠብቀው ነው? የሚጠብቀው ሕዝብ እያለ የት ነው የሚወጣው? ሲሉም ጠይቀዋል። “ማይካድራን ረስቶ እኛን ለዳግም እልቂት ለማጋለጥ የሰላም ዘቡ ይውጣ ማለት ጤነኝነት አይደለም። ሟቾች እያለን ገዳዮች ተገደልን ሲሉ ይሰማሉ። በግፍ ተጨፍጭፈን ያልፋል ብለን ዝም ባልን ለሌላ ግፍ ማዘጋጄት የግፍ ግፍ መገፋት ነው” ብለውናል።
ወይዘሮ ነፃነት ብርሃን በትህነግ የአገዛዝ ዘመን የመናገር መብት አልነበረንም፣ የፈለጉትን መናገር ቀርቶ የፈለጉትን መልበስ አይቻልም ነበር ነው ያሉት። ሳንሞት መቅረታችን የሚያማቸው አካላት አሁንም አካሄዳቸውን ያስተካክሉ፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና መከላከያ ባይደርስ ኖሮ የማይካድራው እልቂት እኛ ላይም ይቀጥል ነበር ነው ያሉት። አሁን ደስታ ላይ ነን በሰላማችን መደሰት ይቻላል፣ በሰላማችን ላይ ቁማር መጫወት ግን አይቻልም ብለዋል።
አሁን ነፃነት ላይ ነን። ከገደለን ጋር ሳይሆን ከሞተልን ጋር እየኖርን ነውም ብለውናል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ነዋሪዎች ነፃነታቸውን ይወዱታል፤ ያከብሩታል፤ ይጠብቁታል፤ ነፃነትን አጥተው አይተውታልና። ሊነጥቃቸው የሚሻውን ይቃወሙታል፤ የተወሰደውን ማንነት ለማስመለስ ረጅሙን መንገድ ተጉዘው አግኝተውታል። እንዳያጡትም አብዝተው ይጠብቁታል፤ በመከራችን ጊዜ ስለ ነፃነት ያልተባበረ በነፃነታችን ጊዜ ስለ መከራችን ቢተባበር እንታዘበዋለን፤ እንቃወመዋለን፤ እንታገለዋለን ብለዋል ሁሉም በአንድ ድምጽ።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የኮሮናቫይረስ ለመከላከል የወጡ ሕጎችን ተግባራዊ በማያደርጉ ዜጎች ላይ የጸጥታ መዋቅሩ ሕግ እንዲከበር ይሠራል” የአማራ ክልል የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ
Next articleየዲከረንስ ችግኝ በመትከል ተጠቃሚ መሆናቸውን በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የፋግታ ለኮማ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡