“የኮሮናቫይረስ ለመከላከል የወጡ ሕጎችን ተግባራዊ በማያደርጉ ዜጎች ላይ የጸጥታ መዋቅሩ ሕግ እንዲከበር ይሠራል” የአማራ ክልል የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ

96
“የኮሮናቫይረስ ለመከላከል የወጡ ሕጎችን ተግባራዊ በማያደርጉ ዜጎች ላይ የጸጥታ መዋቅሩ ሕግ እንዲከበር ይሠራል” የአማራ ክልል የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ እስከ ግንቦት 12/2013 ዓ.ም በ268 ሺህ 35 ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፤ 4 ሺህ 48 ሰዎች ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ፣ በክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ መምሪያ “ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19” በሚል መሪ ሃሳብ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል፡፡ በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶችን እያስከተለ ነው፡፡ ቫይረሱ ብዙ ሰዎችን ለህልፈት እየዳረገ በመምጣቱ ከምንግዜውም በላይ ጥንቃቄ ያሻል ብለዋል፡፡
በምንገኝበት ሀገራዊ ሁኔታ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአስደንጋጭ መልኩ እየጨመረ ቢመጣም ዜጎች ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ደግሞ እየገጠመ ለሚገኘው ችግር የማይመጥን መኾኑን ኀላፊው አንስተዋል፡፡
ኹሉም የሥራ ኀላፊ፣ ባለሙያ፣ ሕዝብና አጋር አካላት የችግሩን አሳሳቢነት በማስተዋል በኀላፊነት ስሜት ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ኮሮናን የመከላከል ሥራ ለአንድ ወገን የሚተው ተግባር ሳይሆን የኹሉን ትብብር እንደሚጠይቅ ነው የጽሕፈት ቤት ኀላፊው የገለጹት፡፡ በተለይም የጸጥታው ዘርፍ የወጡ ሕጎች ተግባራዊ እንዲኾኑ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉቀን አየሁ “እየተፋዘዘ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቅድመ መከላከል ለማነቃቃት የኹሉንም ርብርብ ይጠይቃል” ብለዋል፡፡ የመከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ በመተግበር ሕዝቡን ከወረርሽኙ መታደግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
ኹሉም ተቋማት የመከላከል ሕጎችን ለመተግበር በየደረጃው ከሚገኙ የሥራ ኀላፊዎችና ሠራተኞች ጋር መወያየት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ ወደ ተቋማት የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳይለብሱ የሚሄዱ ማንኛቸውም ተገልጋዮች አገልግሎት እንደማያገኙ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኀላፊ ገደቤ ኃይሉ ወረርሽኙን መከላከል የሚቻለው ኹሉም ዜጋ የተቀመጡ ሕጎችን መተግበር ሲችል ነው ብለዋል፡፡ ሕጎችን ተግባራዊ በማያደርጉ ዜጎች ላይ የጸጥታ መዋቅሩ ሕግ እንዲከበር ይሠራል ብለዋል፡፡ ዜጎችም ከሕግ ተጠያቂነትና ከወረርሽኙ ራሳቸውን ለማዳን ቅድመ መከላከል ዘዴዎችን በአግባቡ መተግበር እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የወጡ ሕጎችን በመተግበር የጸጥታውን መዋቅር ማገዝ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማእከል ሥራ አስጀመረ።
Next article“…ለወራት ያጣጣምነውን ነፃነት ለዓመታት ማጣጣም ስለምንሻ የአማራ ልዩ ኀይልንና ሚሊሻ አይንኩብን”የአካባቢው ነዋሪዎች