ኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማእከል ሥራ አስጀመረ።

586

ኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማእከል ሥራ አስጀመረ።

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም የኢንፎርሜሽን ቴከኖሎጂ እና የኔትወርክ መሠረተ ልማትን የሚያፋጥን ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማእከል በዛሬው እለት ሥራ አስጀምሯል።

ማዕከሉ በከፍተኛ ደረጃ የኀይል ፍጆታን የሚቀንስ፣ በቀላሉ ፍላጎትን ተከትሎ ሊስፋፋ የሚችል እና ፈጣን የሲስተም ተከላ ለማድረግ የሚያስችለው እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ማእከሉን መርቀው በይፋ ዛሬ ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር “እየጨመረ ላለውን የግልና የመንግስት ተቋማት የመረጃ ክምችትና ስርጭት ጥራቱን የጠበቀ የመረጃ ማእከል መገንባት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራር ይህንን ፍላጎት ማስተናገድ እንዳልቻለ አስታውሰው፤ ማዕከሉን መገንባት እንዳስፈለገ ጠቅሰዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞቹን መሰረት አድርጎ ማዕከሉን እንደገነባም ጠቁመዋል።

ማእከሉ ኩባንያው ለሚሰጠው ለሁሉም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የኔትወርክ መሠረተ ልማቶች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኩባንያው የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በፍጥነት ተደራሽ እንዲሆኑ እንዲሁም የኀይል፣ ፍጆታው ያነሰና ለጥገና የሚወጣውን ወጪ 35 በመቶ እንደሚቀንስም ገልጸዋል።

በቅርቡ የተዋወቀው ‘ቴሌብር’ የተሰኘው አገልግሎትም በዚሁ ማእከል ምክንያት ለሥራ ይበቃል ብለዋል።

መሰል ማእከላት በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገነቡም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።

ማእከሉ ለኩባንያው ትልቅ አቅም የሚፈጥር እና በቀጣይ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ የሚረዳ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በቀጣይ በነባሩ የመረጃ ማእከል ላይ ያሉ ደንበኞችም በዚህ ሲስተም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመላክተዋል።

ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሁለት ወራት እንደፈጀና ለዚህም 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ወጪ እንደተደረገበት ተገልጿል።

የሞጁላር መረጃ ማዕከል ክላውድ ሲስተምን ማጎልበት፣ ቨርቹዋል ማድረግ፣ የዳታ ማእከልን የአገልገሎት አሰጣጥ ብቃት ለማሳደግ እንዲሁም የመረጃ ማዕከላትን አሠራር ማዘመን፣ ፈጣንና ውጤታማነት ማሻሻል፣ የኃይል ፍጆታን መቀነስ ከአይነተኛ ጠቀሜታዎቹ መካከል ናቸው። ዘገባው የኢዜአ ነው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ በአምበሳሜ ከተማ 44 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የምግባሩ ከበደ መታሰቢያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመረቀ፡፡
Next article“የኮሮናቫይረስ ለመከላከል የወጡ ሕጎችን ተግባራዊ በማያደርጉ ዜጎች ላይ የጸጥታ መዋቅሩ ሕግ እንዲከበር ይሠራል” የአማራ ክልል የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ