በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ በአምበሳሜ ከተማ 44 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የምግባሩ ከበደ መታሰቢያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመረቀ፡፡

874
በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ በአምበሳሜ ከተማ 44 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የምግባሩ ከበደ መታሰቢያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመረቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ በአምበሳሜ ከተማ በቀድሞ የክልሉ አመራር ምግባሩ ከበደ የተሰየመ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመርቋል።
ወይዘሮ የዝና ግዛው በደራ ወረዳ የተራራ ቤት አርባ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ሆስፒታሉ ሲገነባ በስንቅና በጉልበት ሲደግፉ እንደነበር ተናግረዋል። ከሆስፒታሉ ግንባታ በፊት ለህክምና እስከ ባሕር ዳር ድረስ በመመላለስ ጊዜና ገንዘባቸውን ሲያባክኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የደራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል ዑመር የወረዳው ሕዝብ በርካታ የልማት ጥያቄዎችን ለዓመታት ሲያነሳ ቢቆይም ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ የተለያዩ የመሠረተ ልማቶች ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ግን የሐሙሲት-ስማዳ አማራ ሳይንት የአስፋልት መንገድ ግንባታ ጅማሮ፣ የሐሙሲት የከተማ አስተዳደር መዋቅር መፈቀድ ለሕዝቡን ጥያቄ ከተመለሱት ውስጥ መሆናቸውን ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።
“ዛሬ የተመረቀው የምግባሩ ከበደ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለዓመታት ሲነሳ የነበረው የሕዝብ ጥያቄ የተመለሰበት የልማት ሥራ ነው” ብለዋል።
ዛሬ የተመረቀው ሆስፒታል ለአገልግሎት ብቁ እንዲሆን ባለሙያዎችና ቁሳቁስ ሊሟሉለት እንደሚገባም አቶ ጀማል ጠይቀዋል።
አቶ ጀማል ለሆስፒታሉ ግንባታ የመብራትና አማካሪ አገልግሎቶችን ጨምሮ 44 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት መሆኑን አመላክተዋል።
ዛሬ የተመረቀው የምግባሩ ከበደ መታሰቢያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታው በ2011 ዓ.ም ነበር የተጀመረው፡፡ ከ334 ሺህ ሕዝብ በላይ አገልግሎት እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
በሆስፒታሉ ምረቃ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) ግንባታው የተጠናቀቀው ሆስፒታል ሕይወትን የሚሰጡ እናቶች ሕይወታቸዉን የማይነጠቁበት ቦታ ለማድረግ ታስቦ የተገነባ ነው ብለዋል።
ለዘመናት የሕክምና አገልግሎት በአቅራቢያው አጥቶ በበሽታ ሲሰቃይ የነበሩ የአካባቢው አርሶአደሮች ዛሬ የተመረቀው ሆስፒታል መፍትሔ የሚሰጣቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።
“ሆስፒታሉ ተገንብቶ ቢጠናቀቅም የተሟላ ቁሳቁስ ስለሚያስፈልገው ነዋሪውና ባለሀብቱ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ” ነው ያሉት።
በሆስፒታሉ የሚሠሩ ባለሙያዎች ሕዝቡን በሚገባ ሊያገለግሉ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሆስፒታሉ የክልሉ፣ የዞኑና የወረዳው ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል።
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ከዛሬ ጀምሮ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የወጣውን ሕግ በማይተገብሩ አካላት ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” የክልሉ የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ግብረ ኃይል
Next articleኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማእከል ሥራ አስጀመረ።