
“ከዛሬ ጀምሮ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የወጣውን ሕግ በማይተገብሩ አካላት ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” የክልሉ የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ግብረ ኃይል
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከዛሬ ጀምሮ የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል የወጣውን መመሪያ የማስተግበር ሥራ የሚሠራ መኾኑን የክልሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) ተናገሩ፡፡
“ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19” በሚል መሪ ሐሳብ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል፡፡ “ከዛሬ ጀምሮ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የወጣውን ሕግ በማይተገብሩ አካላት ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል ሰብሳቢዋ፡፡
በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) የንቅናቄ መድረኩ እየተቀዛቀዘ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ሥራ እንደገና ለማስጀምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዜጎችን ከወረርሽኙ መጠበቅ ግዴታ በመኾኑ ከዛሬ ጀምሮ ኹሉም የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና ግለሰቦች በኹሉም እንቅስቃሴዎች ወረርሽኙን ለመከላከል የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ለብሰው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማትና ግለሰቦች ደግሞ በመመሪያ 30/2013 መሠረት ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት፡፡
ዜጎች ሕጉን መተግበር ያለባቸው ተገደው ሳይኾን እስትንፋሳቸውን ለማቆየት እንደሆነ በመረዳት መሆኑን ዶክተር ሙሉነሽ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭት ከአፍሪካ በአራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝና ወረርሽኙ እየጨመረ ከመጣባቸው ሀገራት መካከል እንደምትገኝም ጠቅሰዋል፡፡ በጽኑ አፍላ ሕሙማን ደረጃ ደግሞ ኢትዮጵያ ከመላው አፍሪካ በአንደኛ ደረጃ ትገኛለች ብለዋል፡፡
ዶክተር ሙሉነሽ እንደገለጹት በአማራ ክልል በቀን ከ70 ያላነሱ ሰዎች በወረርሽኙ ይያዛሉ፤ በቀን ሁለት ሰዎች ይሞታሉ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ የጤና ተቋማትም ታማሚዎችን ከሚሸከሙት አቅም በላይ ደርሰዋል፤ ወደ ጽኑ ሕሙማን የሚገቡ ሰዎችም አስፈላጊ ሕክምና ሳያገኙ እየሞቱ ነው፤ ጤና ተቋማት ሳይደርሱ የሚሞቱ ሰዎች በዝተዋል፡፡
ማኅበረሰቡ የወረርሽኙን አሳሳቢነት በመረዳት የቅድመ መከላከል እርምጃዎችን በአግባቡ ሊተገብር ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይም ዜጎች የ”መ” ሕጎችን ማለትም ማስክ መልበስን ፣ ርቀት መጠበቅን፣ መታጠብን እና መከተብን መተግበር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰዎች በማንኛውም ቦታ ምክንያት ሳያስፈልጋቸው ማስክ መልበስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ይህንን በማይተገብር ዜጋም እስከ ፅኑ እስራት የሚያደርስ ቅጣት የሚተላልፍ መኾኑን አውቆ መተግበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የተቋማት የሥራ ኀላፊዎችም ከራሳቸው ጀምረው የተቋሙ ሠራተኞች እንዲተገብሩ በትልቅ ኀላፊነት ሊሠሩት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ተቋማት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተግባርን አካቶ በመሥራት የተልዕኳቸው አንድ አካል ማድረግ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡ የጸጥታና የፍትሕ ተቋማት ሕጉ እንዲከበር ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ጠንካራ የመከላክል ሕግ ተግባራዊ ያደረጉት ሀገራት ወረርሽኙን መግታት እየቻሉ መሆናቸውን ዶክተር ሙሉነሽ አንስተዋል፡፡ ኅብረተሰቡም የጤና ባለሙያዎችን ምክር መተግበር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ