“አሜሪካ ከመታሰሷ አስቀድሞ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ የሚኖርበት፣ መንግሥት ያለበት የሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ሆኖ የኢትዮጵያ ምድር መሆኑ ይታወቃል” ታሪክ አዋቂ

630
“አሜሪካ ከመታሰሷ አስቀድሞ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ የሚኖርበት፣ መንግሥት ያለበት የሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ሆኖ የኢትዮጵያ ምድር መሆኑ ይታወቃል” ታሪክ አዋቂ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ስለ አንተ እኔ ልናገር፣ ስምህን አንተ ሳይሆን እኔ አውቀዋለሁ፣ ማንነትህን ለክቼ እሰጥሃለሁ፣ የተሰጠህን ማንነት ተቀብለህ ትለብሳለህ፣ እንቢኝ ያልክ ጊዜ ወዮልህ ማደሪያህ ጨለማ ይሆናል፣ መዳረሻህ እስራት ወይንም ሞት ነው የአሸባሪው የትህነግ አስተሳሰብ ነበር።
እውነት ከውሸት መካከል ጠርቶ ይወጣል እንጂ ጠፍቶ አይቀርም። እውነትን አስሮ የሚያስቀር ታይቶም አይታወቅም። የውሸት ዘመን አላፊ ነው። የእውነት ዘመን ግን ዘላለማዊ ነው። እውነትን የያዘ አይሸነፍምና በትህነግ የታሠረው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ በእውነት ነፃ ወጣ። የተበደለውን ነፃ ያወጣች እውነት በዳዩን አሰረችው። ገሚሱን ስታጠፋው፣ ገሚሱን እንደ ዱር እንስሳ በሸርጥ ስር እንዲኖር ፈረደችበት።
ከእውነት ጋር የዘመተ ዘማች ድሉ ይዘገይበት እንደሆነ እንጂ ያለ ድል አይመለስም። ተፈጥሮ ያወጣለትን፣ ታሪክ የመዘገበለትን፣ ሀገር ያወቀለትን ስሙን ነጥቆ ሌላ ስም ሰጥቶ መኖር ምን የሚሉት ይሆን? የሚታወቅበት ማንነት፣ የማይደበዝዝ እውነት አለው። በቤቱ እንግዳ ሆኖ፣ ለዚያውም ሳይሰተናገድ የኖረ ነው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ። ሰው በቤቱ ቢቻል አስተናጋጅ ባይችል ግን ተስተናጋጅ መሆን ነበረበት። በወልቃይት ግን ይህ አልነበረም።
ከያኒያን፣ የታሪክ ሰዎች፣ ተጓዦችና ሌሎችም ጎንደርን ሲያነሱ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራን ሳያነሱ አያልፉም። ለምን ካሉ ጎንደር ሲነሳ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ካልተነሳ ሙሉ አይሆንምና ነው። ስለ ጎንደር የተሟላ ታሪክ ለመጻፍ፣ የተሟላ ዘፈን ለመዝፈን፣ የተሟላ ጉብኝት ለማድረግ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራን ማካተት ግድ ነው። የነጠረ እውነት እያለ ታዲያ አሸባሪው ትህነግ የጎንደርን አካል ቆርጦ ከትግራይ ክልል ጋር ለጥፎት ኖረ።
ጊዜ ደጉ ያነሳውን እየጣለ፣ የጣለውን እያነሳ በጨለማ የተጀቦነ የሚመስለውን እውነት አውጥቶ በአሻገር አሳዬው። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ እውነት ተገለጠ። ውሸትም ተጋለጠ።
በወልቃይት ጠገዴ የእውነት ዳስ ቢጣልም የውሸት አሳላፊዎች ዳሱን ለመበጥበጥ ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ። የሚገርመው ለሠረጉ ያልተጠሩት ኹሉ ስለ ዳሱ ይናገራሉ። ዳሩ የወልቃይት ዳስ የተሠራበት እውነት ላይ ነውና በዳሱ ይዘፈንበታል እንጂ አይለቀሰበትም። የለቅሶው ዘመን አልፏልና።
ሹምዬ ወልደ ሥላሴ ይባላሉ። የራስ ቢትወደድ አዳነ የልጅ ልጅ ናቸው። የታሪክ ሰውም ናቸው። ራስ ቢትወደድ አዳነ ጣልያንን በጥይት መትተው ካባረሩ የሰሜን በጌምድር አርበኞች መካከል አንደኛው ናቸው። እኒህ ታላቅ አርበኛ ከጣልያን ማክተም ማግሥት እስከ ዘመነ ደርግ መባቻ ድረስ የዳባት አውራጃ አስተዳዳሪ ነበሩ። ዳባት አውራጃ በሥሩ ከሚያቅፋቸው አካባቢዎች መካከል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አንደኛው ነው። የእኒህ ሰው የልጅ ልጅና ታሪክ አዋቂው ሹምዬ ወልደ ሥላሴ ስለ ወልቃይት እውነት ነግረውናል።
ከ1934ዓ.ም እስከ ንጉሡ ውድቀት ድረስ ወልቃይት ጠገዴ በአያቴ በራስ ቢትወደድ አዳነ ይተዳደር ነበር። ከጎንደር ሑመራን መንገድ ያሠሩትም ራስ ቢትወደድ አዳነ ናቸው። ሑመራ ላይ ሰፊ የእናቴ እርሻ ነበር። እርሻችን በአምስት በስድስት ትራክተር የሚታረስ ነበር። እኔም አያቴን እየተከተልኩ የክረምቱን ጊዜ የማሳልፈው ሑመራ ነበር። አካባቢው የአማራ ስለመሆኑ እኔ ማስረጃ ነኝ ነው ያሉት። በወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ሀገሮችና ተቋማት ስለሚያሳድሩት ጫና ሲናገሩም “አሜሪካ ከመታሰሷ አስቀድሞ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ የሚኖርበት፣ መንግሥት ያለበት የሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ሆኖ የኢትዮጵያ ምድር መሆኑ ይታወቃል” ነው ያሉን። አሸባሪው ትህነግ ሲነሳ የአማራን ለም መሬቶች መውሰድ፣ አማራን ማጥፋትና መስፋፋት መሠረት አድርጎ ስለተነሳ እንጂ ከተከዜ ማዶ የሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት እንጂ ትግራይ የሚባል ግዛት የለም ነው ያሉን።
ኢትዮጵያ ሀገር እንዳትሆን የሚፈልጉ ኃይሎች የትህነግን የውሸት ታሪክ ለራሳቸው ጥቅም እንደሚጠቀሙበትም ነግረውናል። “በመሠረቱ የአማራ ልዩ ኃይል በትግራይ መሬት ውስጥ የለም። ምዕራብ ትግራይ የሚባለው አዲ አቦ፣ ሽሬና ሽራሮ ነው። በዚህ አካባቢ የአማራ ልዩ ኃይል የለም። የአማራ ልዩ ኃይል ያለው በራሱ መሬት ላይ ነው፤ ባለበትም የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት እየጠበቀ ያለ እንጂ ወራሪ ኃይል አይደለም” ነበር ያሉን።
የፌዴራሉም ሆነ የአማራ ክልል መንግሥት የአማራ ልዩ ኃይል ከተከዜ መለስ እንጂ በምዕራብ ትግራይ አለመኖሩን ግልፅ አድርገው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስረዳት አለባቸው ነው ያሉት። የውጭ ኃይሎች በውስጥ ጉዳይ ስለ ሚያወሩት ጉዳይም “በኢትዮጵያ ላይ ብዙ ወረራዎች ተካሂደዋል። ነገር ግን አንደኛውም አልተሳካም። ይህም የሆነው ኢትዮጵያውያን ለሉዓላዊነትና ለሰንደቃቸው ባላቸው ፅኑ ፍቅር ነው። አሁንም በሉዓላዊነታችን ጉዳይ አንድ መሆን አለብን” ነው ያሉት። ቀደም ባለው ዘመን ጀምሮ ባንዳዎች እንደነበሩ የተናገሩት የታሪክ አዋቂው የውጭ ኃይሎች ዓላማቸውን ለማሳካት እየተጠቀሙባቸው መሆናቸውንም ነግረውናል።
ኢትዮጵያ የአርበኝነት እንጂ የባንዳነት ታሪክ የላትም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድ ኾነው ነው ሉዓላዊነታቸውን አስጠብቀው የኖሩት። ትህነግ ያመጣው ሴራም ኢትዮጵያውያን የመፈተን እንጂ የማፍረስ አቅም የለውም ነው ያሉን። በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጉዳይ ጥያቄ የለም። የአያቶቻችንን አፅም ይዎቅሰናልም ነው ያሉት። የወልቃይትን ጉዳይ እንኳን ተራ ሽፍታ ኾነው ይቅርና መንግሥት እያሉም አላሸነፉትም ነው ያሉት። መስፋፋት እንጂ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ የአማራ መሬት መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉም ነው ያሉት።
በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ፕሮፓጋንዳ መረበሽ እንደማያስፈግም ተናግረዋል። የአማራ ልዩ ኃይል የተቀማውን እውነት ነው የተቀበለውም ብለውናል።
ሌላኛው የአካባቢው ታሪክ አዋቂ ባዩ በዛብህ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራን የማውቀው በሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ነው። ሕወሓት መራሹ መንግሥት ከገባ ጀምሮ ሕዝብ ሳይጠየቅ ወይም የወሰን ጥናት ሳይደረግባት ዝም ብሎ የተከለለ ነው ብለዋል። በወቅቱ ተቃውመው እንደነበር ያነሱት ታሪክ አዋቂው የጎንደር ልማት ማኅበር ምክትል ሰብሳቢ ነበርኩ፣ ማኅበሩ የሚንቀሳቀሰው በሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ነበር፣ ትህነግም እኛ በምንቀሳቀስበት ሥፍራ ክልል ብለው ስለመጡ ተጣልተናል ነው ያሉት። ተከዜን ተሻግረው መምጣታቸው ትልቁ ስህተት ነው ብለዋል።
ሀገራቱ ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩት ጫና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ መሆኑንም ተናግረዋል። መንግሥትና በመላው ዓለም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ኹሉ እንደ ዓድዋና እንደ ካራማራ ኹሉ በአንድነት መቆም አለበት ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ወቅት ምንም አይነት ማታላያዎችን መስማት እንደማይገባምው ተናግረዋል። ኢትዮጵያን እየተዋጋት ያለው ገንዘብ ነው ያሉት የታሪክ አዋቂው ታላቅ ታሪክ ያላትን ሀገር ለማስቀጠል በአንድነት መቆም ይገባልም ብለዋል።
የወልቃይት እውነት የትናንት፣ ከትናንት ወዲያ ያለው እውነት ታሪክን እየጠቀሰ፣ መረጃ እያጣቀሰ የሚቀርብ ነው። ስለ ወልቃይት እውነት ታሪክ ይዘክራል። የነበረ፣ ያለ ይመሰክራል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ለ680 የተደራጁ አርሶ አደሮች የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮችን ድጋፍ አደረገ፡፡
Next articleየኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች ጠየቁ፡፡