ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ለ680 የተደራጁ አርሶ አደሮች የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮችን ድጋፍ አደረገ፡፡

222
ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ለ680 የተደራጁ አርሶ አደሮች የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮችን ድጋፍ አደረገ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የሊቦ ከምከም አካባቢ ፕሮግራም በወረዳው ለ680 የተደራጁ አርሶ አደሮች ነው 136 የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮችን ድጋፍ ያደረገው፡፡
በድጋፉ ርክክብ ላይ ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል በወረዳው የካብ ቀበሌ ነዋሪ ደመላሽ እንደሻው በግብረ ሰናይ ድርጅቱ ድጋፍ የተደረጉላቸው የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮች የመስኖ እርሻ ሥራቸውን በተሻለ መልኩ እንዲከውኑ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል፡፡
ሌላኛዋ አርሶአደር ወይዘሮ ምግባር ደፋሩ የመስኖ እርሻን በባሕላዊ መንገድ ይከውኑ እንደነበር ገልጸው ድጋፉ ዘመናዊ አሠራር እንዲከተሉ እና የተሻለ ለማምረት እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡ ይህም ቤተሰቦቻቸውን በተሻለ ሁኔታ ማስተዳደር እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል፡፡ ለተደረገላቸው ድጋፍም አመስግነዋል፡፡
በድጋፍ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱሰትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የአካባቢውን ሕዝብ የልማት ፍላጎት ለማገዝ መሥራቱንና ለዘላቂ ልማት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ አርሶ አደሩም የተደረገለትን ድጋፍ በአግባቡ ለልማት እንዲጠቀምበት አሳስበዋል፡፡
አቶ መላኩ አክለውም ለዘላቂ ልማት የሰላምን አስፈላጊነት በመግለጽ ኅብረተሰቡ ችግሮችን ለመፍታት አንድነቱንና ሰላሙን መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የሊቦ ከምከም አካባቢ ፕሮግራም ለወረዳው ልማት በባለቤትነት እና በተነሳሽነት በመሥራት ኅብረተሰቡ ከችግር እንዲላቀቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በድጋፍ የተገኙትን የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮች በአግባቡ በመጠቀም አርሶ አደሮቹ ዘላቂ ውጤት እንዲያገኙ ማድረግ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኀላፊዎች ኀላፊነት መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል፡፡
በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የጎንደር ጉድኝት አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ አባተ የአካባቢው አርሶ አደር በክረምት ወቅት በሚከሰት ጎርፍ ጉዳት ምክንያት የመኸር እርሻው ላይ እንቅፋት እንደሚፈጠርበት ጠቅሰዋል፡፡ ድጋፉ ይህንን የምርት እጦት ለማካካስ በበጋ የመስኖ እርሻ ሥራ በተሻለ መልኩ እንዲፈጽም ለማገዝ ታስቦ የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ – ከአዲስ ዘመን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleመንግሥት ተፈናቃዮችን በልዩ ሁኔታ ለማቋቋም የወሰደውን አማራጭ እንደሚደግፉት የተፈናቃይ ተወካዮች ተናገሩ።
Next article“አሜሪካ ከመታሰሷ አስቀድሞ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ የሚኖርበት፣ መንግሥት ያለበት የሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ሆኖ የኢትዮጵያ ምድር መሆኑ ይታወቃል” ታሪክ አዋቂ