መንግሥት ተፈናቃዮችን በልዩ ሁኔታ ለማቋቋም የወሰደውን አማራጭ እንደሚደግፉት የተፈናቃይ ተወካዮች ተናገሩ።

115
መንግሥት ተፈናቃዮችን በልዩ ሁኔታ ለማቋቋም የወሰደውን አማራጭ እንደሚደግፉት የተፈናቃይ ተወካዮች ተናገሩ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በመተከል ዞን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች የጸጥታ ስጋት በሌለባቸው አካባቢዎች አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደየቀያቸው እንደሚመለሱ የሁለቱ ክልሎች የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል።
ተፈናቃዮችን በልዩ ሁኔታ ለመመለስና ለማቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስመልክቶ ራንች ከሚገኙ የተፈናቃይ ተወካዮች ጋር ውይይት ተደርጓል።
የአማራ ክልል ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶክተር)፣ የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኀይል ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አሥራት ዴኔሮ እና የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጋሹ ዱጋዝ ጉዳዩን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት ተፈናቃዮችን ለመመለስና ለማቋቋም መግባባት ላይ መድረሳቸውን ዶክተር ሰማ ተናግረዋል።
በውስን ቦታ ሲኖሩም አስፈላጊ የኾኑ ማኅበራዊ ተቋማት ይሟላሉ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ኀይል በመንግሥት ቁጥጥር ሥር እስከሚውል ድረስም ቋሚ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፤ እራሳቸውን ከጥቃት መከላከል የሚችሉበት ሁኔታም ይመቻቻል ብለዋል።
ተፈናቃዮችን ለመመለስና ለማቋቋም ጥረት እንደሚደረግም የመተከል ዞን አስተዳዳሪ ጋሹ ዱጋዝ አረጋግጠዋል። በሂደት ደግሞ በቋሚነት ወደየአካባቢያቸው እንዲመለሱ ይደረጋል ብለዋል።
ታጣቂ ኀይሎች የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እየገቡ መኾኑን ደግሞ ሌተናል ጄኔራል አሥራት ዴኔሮ አስገንዝበዋል። የሰላም ጥሪውን የተቀበሉት በዞኑ አምስት ወረዳዎች ጫካ የገቡ ሽፍቶች ናቸው፣ አብዛኛዎቹ የሽፍታ ቡድን መሪዎች ጥሪውን በመቀበል የተሐድሶ ስልጠና እየተሰጡ መኾኑን አብራርተዋል።
በሂደቱ ጥርጣሬ እንዲፈጠር የሚፈልጉ አካላት የውዥንብር ወሬ እየነዙ ቢኾንም ሁኔታውን ለማስተካከል በተደረገ ጥረት ጥሩ ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል። በዚህም በስጋት አካባቢያቸውን ጥለው ጫካ የገቡ የጉሙዝ ማኅበረሰብ ወደየ አካባቢያቸው እየተመለሱ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሌተናል ጄኔራል አሥራት ዴኔሮ በቻግኒ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የተጀመረው ጥረትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። የሁለቱ ክልል መንግሥታት የጀመሩት የጋራ ሥራ ለጸጥታ ተግባሩ ያግዛል ያሉት ሌትናል ጄኔራሉ ተፈናቃዮችን ለመመለስ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለውም አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም በሕዝብ መካከል አንድነት እንዳይኖር፣ በጥርጣሬ እንዲተያዩ የሚሹ አካላትን ማጋለጥና በጋራ መጋፈጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የተፈናቃይ ተወካዮችም በልዩ ሁኔታ ለማቋቋም የተወሰደውን አማራጭ እንደሚቀበሉት ተናግረዋል።
መንግሥትን በተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚያግዝ ሕዝብ ተረጅ መኾኑ እንዳሳዘናቸው የተናገሩት ተፈናቃዮቹ የእርሻ ጊዜ እያለፈ በመሆኑ በፍጥነት ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በኋላም የመንግሥት ተረጂ መኾን እንደማይፈልጉ እና ሠርተው መብላት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ኾነው ሕዝብ እንዲጎዳ የሚሠሩ አካላትን መንግሥት በአፋጣኝ አጥርቶ ሕጋዊ እርምጃ ካልወሰደ ችግሩ ሊቆም እንደማይችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተቀምጠው ሕዝቡ እንዲጎዳ፣ንብረቱ እንዲወድም እና እንዲፈናቀል የሚሠሩ አካላትን መንግሥት እልባት ሊሰጣቸው ይገባልም ብለዋል፡፡
በተፈናቃዮች ውስጥም ኾነ ከተፈናቃዮች ውጭ ኾነው በሕዝብ ሽብር የሚነዙ ሰዎች ላይም መንግሥት ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ የተፈናቃይ ተወካዮች ጠይቀዋል፡፡
በሽፍትነት ጫካ ውስጥ ተደብቀው በሕዝብ ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉ ሰዎችን በተጀመረው አግባብ የማግባባት ሥራ መሠራቱ እንዲቀጥል ካልኾነ የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ የተፈናቃይ ተወካዮች አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ-ከቻግኒ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበመጭው ክረምት ወቅት በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከ30 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች እንደሚተከሉ የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
Next articleወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ለ680 የተደራጁ አርሶ አደሮች የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮችን ድጋፍ አደረገ፡፡