በመጭው ክረምት ወቅት በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከ30 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች እንደሚተከሉ የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

227
በመጭው ክረምት ወቅት በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከ30 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች እንደሚተከሉ የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2013 ዓ.ም (አሚኮ)የአፍሪካ ምድር ጣራ፣ የብዝኃ ሕይዎት ጓዳ፣ የብርቅዬ እንስሳቶች መካን እና የዓለም ቱሪስቶች ተናፋቂ ነው – የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ፡፡ ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ እንደሰንሰለት ከተንሰላሰሉት ተራሮቹ ጋር እኩል የተመልካችን ቀልብ የሚማርኩት የብዝኃ ሕይዎት ሃብቱ እና ብርቅዬ እንስሳቱ ለጎብኝዎች ሃሴትን ይሰጣሉ፡፡
በ2013 ዓ.ም ክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ30 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታትም ከ83 ሺህ በላይ ችግኞች በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ተተክለዋል ተብሏል፡፡
ፓርኩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ውጣ ውረዶችን አስተናዷል፡፡ የዓለምን ቱሪዝም ክፉኛ የጎዳው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና በፓርኩ ውስጥ የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፈውበታል፡፡ ከነዚህ ፈተናዎች ጋር እየታገለ ያለው ፓርኩ በ2011 ዓ.ም የደረሰበትን ቃጠሎ ጉዳት ለመተካት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ83 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች መተከላቸውን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ አበባው አዛናው ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡ በተለይም በ2011 ዓ.ም በፓርኩ ክልል ውስጥ ከተፈጠረው የእሳት አደጋ በኋላ የሀገር በቀል ችግኝ ተከላ መርኃ ግብር በዘመቻ እና በመደበኛ መልኩ ሲካሄድ መቆየቱን ሥራ አስኪያጁ አመላክተዋል፡፡
ዘንድሮም በፓርኩ፣ በዳባት እና በደባርቅ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤቶች የችግኝ ጣቢያዎች የተዘጋጁ 30 ሺህ የሀገር በቀል ችግኞች በፓርኩ ክልል ውስጥ ይተከላሉ ብለዋል፡፡
ከሐምሌ 01/2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር የጉድጓድ ዝግጅት እየተካሄደ ነውም ብለዋል ሥራ አስኪያጁ፡፡
ባለፉት ዓመታት እንደተካሄዱት አይነት ዘመቻዎች በማኅበራት፣ በከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት እና አደረጃጀቶች በፓርኩ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ በመደበኛ መርኃ ግብር የሚደረገው የችግኝ ተከላ ሂደትም ይቀጥላል ብለዋል፡፡
አቶ አበባው እንዳሉት ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት የሀገር በቀል ችግኝ ተከላ መርኃ ግብሮች የመፅደቅ ምጣኔያቸው ጥሩ ነበር፡፡ በተለይም ለተተከሉት ችግኞች ሲባል አካባቢው ከንክኪ ነፃ እንዲሆን መደረጉ ለፓርኩ ህልውና አመች ሁኔታ መፍጠሩን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ፋሲል ከነማ 1 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ቴሌቶን ሊዘጋጅ ነው፡፡
Next articleመንግሥት ተፈናቃዮችን በልዩ ሁኔታ ለማቋቋም የወሰደውን አማራጭ እንደሚደግፉት የተፈናቃይ ተወካዮች ተናገሩ።