
ሀገራዊ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የምርጫ ሂደትን የጠበቀ እንዲኾን ወጣቶች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ወጣቶች ማኅበር ወጣቶችና ምርጫ፣ ወጣቶችና ሰላም፣ ሴቶችና ምርጫ እንዲሁም ወጣቶችና ብዝኃነት በተሰኙ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ምክክር በባሕር ዳር እያካሄደ ነው።
የማኅበሩ አባልና የምክክሩ ተሳታፊ ኢትዮጵያ አሻግሬ መጪው ምርጫ ሰላማዊ እንዲኾን ወጣቱ በመራጮች ካርድ ምዝገባ ወቅት ያሳየውን ተሳትፎ በምርጫው ቀንም ኾነ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ መቀጠል ይኖርበታል ብላለች፡፡
“ምርጫን አስመልክቶ ማንኛውም ጉዳይ በምክክር መፍታት እንጂ ወደ ግጭት ማምራት የለበትም፤ ችግሮች ሲከሰቱ በተረጋጋ መንፈስ ሊፈቱ ይገባል” ብላለች፡፡
የማእከላዊ ጎንደር ዞን የወጣቶች ማኅበር ሊቀመንበር ዳንኤል አወቀ፣ በዞናቸው በሚገኙ ወረዳዎች ከምርጫ ቅስቀሳ ጀምሮ ያለውን ሂደት ለመከታተል የሚያስችል ዕቅድ በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሱ እንደኾነ ተናግሯል፡፡ ምርጫው ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ በፈጠሩት አደረጃጀት እየሠሩ መኾኑን አስረድቷል፡፡ “ወጣቱ ይጠቅመኛል፣ እኔ የምፈልገውን ሥራ ይሠራልኛል ብሎ የሚያስበውን የፖለቲካ ፓርቲ በነፃነት መምርጥ ይጠበቅበታል” ብሏል፡፡
ምርጫው አካታች፣ ዜጎች የሚመርጡና የሚመረጡበት እንዲሆን ወጣቱ የራሱን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መኳንንት መከተ ናቸው፡፡
ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ጤናማ የምርጫ ሂደትን የጠበቀ እንዲኾን ወጣቶች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
የምርጫ ሂደቱና ውጤቱ ሰላማዊ እንዲሆን ወጣቶች የበኩላቸዉን አሻራ ማሳረፍ እንደሚገባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
የአማራ ወጣቶች ማኅበር ሊቀመንበር ዓባይነህ ጌጡ ማኅበሩ ኢትዮጵያ በብዝኃነት የበለጸገች ሀገር ናት፣ ሀገሪቱ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባሕልና ሃይማኖት ባለቤት ስለኾነች ሁሉም ዜጋ ልዩነቶችን ማክበር ይጠበቅበታል ነው ያለው፡፡
የማኅበሩ አባላት ወደ መጡበት ሲመለሱ ለአካባቢያቸው ወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ብሏል፡፡
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ