በጎንደር ከተማ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሴቶች ፍትሐዊ የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት እንደሚሠሩ ገለጹ፡፡

134
በጎንደር ከተማ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሴቶች ፍትሐዊ የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት እንደሚሠሩ ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ባዘጋጀው መድረክ ላይ በ6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ከጎንደር ከተማ እና ከማእከላዊ ጎንደር ዞን ከተውጣጡ ሴት ነጋዴዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ቢመረጡ ለሴቶች በኢኮኖሚ ዘርፍ ሊሠሯቸዉ ያቀዷቸዉን ተግባራትም አስተዋውቀዋል፡፡ በትውዉቁ ላይ ብልጽግና ፓርቲ፣ አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና እናት ፓርቲ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በኢኮኖሚያዊ ማኒፌስቶ ትውውቁ ላይ ብልጽግና በቀጣይ አምስት ዓመታት ከተመረጥኩ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን አከናውናለሁ ብሏል። ሴቶችን ወደ አመራር ሰጭነት ማምጣት፣ ሴቶች በሚፈልጉት ሕብረት ሥራ ማኅበራት እንዲታቀፉ ማድረግ፣ በማምረት ዘርፍ ለተሰማሩ ሴቶች ሙያዊ እገዛ ማድረግ፣ ብድር ማመቻቸት እና ምርታቸዉን ለዉጭ ገበያ እንዲያቀርቡ እሠራለሁ ነው ያለው፡፡
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መዋቅር በየደረጃው ማጠናከር ትኩረት ይሰጠዋልም ብሏል ፓርቲው፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ 6ኛዉን ሀገራዊ ምርጫ ካሸነፍኩ ሴቶች የአመራር ክህሎታቸዉን በመጠቀም እውነተኛ አመራር የሚሰጡበትን መንገድ እንፈጥራለን ብሏል፡፡ ሴቶች በሀገራቸዉ ሠርተዉ ንብረት የማፍራት ደኅንነታቸዉ ተጥብቆ እንዲያመርቱ እንደሚሠራም ገልጿል፡፡ የአካባቢያቸውን ጸጋ በመጠቀም በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የሀገር ዉስጥ ገበያ ትስስር እንዲጎለብት፣ በዝቅተኛ ወለድ ብድር እንዲያገኙ እና ታክስ እንዲቀነስላቸዉ ይሠራል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መጭዉን ሀገራዊ ምርጫ ቢያሸንፍ እኩልነት እንዲሰፍን፣ ነጻ ትምህርት እድል እና የሴት ተማሪዎችን የማቋረጥ ምጣኔን ለመቀነስ እንደሚሠራ አመላክቷል፡፡ ወላጅዎች ሴት ልጆቻቸዉን ወደትምህርት ገበታ እንዲልኩ አስገዳጅ ሕግ ማዉጣት፣ ሴቶችን በተመለከተ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን መቀየር፣ ወንዶችን ያሳተፈ የቤተሰብ ምጣኔ፣ የሴት ልጅ ጥቃት እንዲቀንስ፣ በሴቶች ባለቤትነት የተያዙ የንግድ ተቋማት ታክስ ቅነሳ እንዲደረግላቸዉ እና በዝቅተኛ ወለድ ብድር እንዲያገኙ እንደሚሠራ ገልጿል፡፡
እናት ፓርቲ በበኩሉ ሴቶች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንሠራለን ብሏል፡፡ ለዉክልና ብቻ ሳይሆን ሴቶች ባላቸዉ ብቃት አመራር ሰጭነት ቦታ እንዲያገኙ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡ በመንግሥት ተቋማት ላይ የሕጻናት ማቆያ እንዲኖር፣ በአመራርነት የሚመደቡ ሴቶች ሙያዊ እገዛ እንዲያገኙ፣ የንግድ ሥርዓቱ ከጥቂት ሰዎች እጅ ወጥቶ ብዙዎች እንዲሳተፉበት፣ ከሕገወጥ ደላሎች እንዲጸዳ እንደሚሠራም አመላክቷል፡፡ ሴቶችን የሚያበረታታ በንግድ እቅዳቸዉ ብቻ ያለ መያዣ ብድር እንዲመቻች ይደረጋልም ብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ይርጉ ፋንታ – ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአማራ ክልል በአራት የምጣኔ ሀብት ዘርፎች እስከ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱ ተገለጸ፡፡
Next articleበኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓትን ለማዘመን እየተሠራ እንደሚገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።