
በአማራ ክልል በአራት የምጣኔ ሀብት ዘርፎች እስከ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ አራት የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡ ፍኖተ ካርታውን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት የልማት አማካሪዎች ቡድን የፖሊሲ አማካሪ ወይዘሮ ሰዋረግ አዳሙ እንዳሉት ቡድኑ በክልሉ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ያመጣሉ ተብለው የታመነባቸው ዘርፎች እና ችግሮች ላይ ጥናት አድርጓል፡፡
በዚህም በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በማዕድን ዘርፎች ፍኖተ ካርታው ተዘጋጅቷል፡፡ እነዚህ ዘርፎች ክልሉ ካለው እምቅ ሀብት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለምጣኔ ሀብት ካላቸው አስተዋጽኦ አኳያ መመረጣቸውን ባለሙያዋ ገልጸዋል።
ዘርፎቹ በአምስት ዓመታት ውስጥ እስከ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላሉ ተብሏል፡፡ በእነዚህ ዘርፎች የሚታዩ ችግሮች እንደየ ሴክተሩ ቢለያዩም የመሬት አቅርቦት፣ የብድር፣ የመሠረተ ልማት፣ የኀይል እጥረትና የሕግ ማዕቀፍ የጋራ ችግሮች መሆናቸው ተቀምጧል።
ችግሮቹን ለመፍታትም ፖሊሲዎችን የማስተካከል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተነስቷል። ዘርፎቹ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅርቦት የሚጠይቁ በመሆናቸው በቀጣይ የግል ሴክተሩ ከፍተኛውን ድርሻ እንዲይዝ ማድረግ እንደሚስፈልግም ተመላክቷል።
የሚታዩ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፎችን፣ የመሬት፣ የፋይናንስ እና የሰው ኀይል አቅርቦቶች በተቀናጀ ሁኔታ እንዲሠሩ ማድረግ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ተብሏል። እነዚህ ዘርፎች ውጤታማ እንዲሆኑ የመንግሥትና የአጋር ሴክተር መስሪያ ቤቶች ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግም ተነስቷል።
ፍኖተ ካርታው ለክልሉ ካቢኔ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆንም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ