
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የቀጣናውን ሀገራት በኢኮኖሚ እንደሚያስተሳስር የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለማችን ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር የሚሻገሩ በረካታ ወንዞች አሉ፡፡ ሀገራትም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ለትራንስፖርት፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት፣ ለመስኖ ልማት፣ ለከተሞች ውኃ አቅርቦትና ለሌሎችም ተግባራት ይገለገሉባቸዋል፡፡
እ.አ.አ በ1923 የጸደቀው የጄኔቫ ስምምነት ወንዞችን የሚጋሩ ሀገራት በመካከላቸው ያለመግባባት ቢፈጠር ያለመግባባቶችን በሰላማዊ ድርድር በመፍታት ለጋራ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መሥራት እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡
የኃይል አቅርቦት ችግርን እንደሚፈታ እና ከድኅነት እንደሚያወጣ ተስፋ የተጣለበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ለቀጣው ሀገራት የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ መኾኑን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አንዳርጋቸው ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችው ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለቀጣናው ሀገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ረዳት ፕሮፌሰር አንዳርጋቸው ያብራሩት፡፡
ኢትዮጵያ በዋናነት ታላቁን የህዳሴ ግድብ እየገነባች ያለቸው ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለዜጎቻቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ማድረግ ላልቻሉ የጎረቤት ሀገራት ጭምር አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሂደትም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማጠናከርና ለመደጋገፍ ያግዛቸዋል ነው ያሉት ምሁሩ፡፡
የግድቡ መጠናቀቅ ከዓለም በርዝመቱ የመጀመሪያ የኾነውን የዓባይ ወንዝ ሁሉም የወንዙ ተጋሪ ሀገራት የውኃውን ሀብት በጋራ እንዲያስተዳድሩትና የውኃውን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ መነሳሳት እንደሚፈጥርም አስረድተዋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከኤሌክትሪክ ጠቀሜታው በተጨማሪ የንግድና የመዝናኛ ማዕከል በመኾን ለቀጣናው ሀገራት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝም ረዳት ፕሮፌሰር አንዳርጋቸው ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያም በዓባይ ወንዝ ከግብፅ እየለማ የሚመጣውን ፍራፍሬ በውጭ ምንዛሬ እየገዛች መሆኑን ጠቅሰው የግድቡ መጠናቀቅም ይህን ችግር ከመፍታት ባለፈ ሀገራት ይበልጥ በንግድ ዘርፍ ጠንካራ ትስስር እንዲኖራቸው ያግዛል ብለዋል፡፡
ሌላው የግድቡ መጠናቀቅ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1929 በታላቋ ብሪታኒያና በግብፅ መካከል የተደረገው ስምምነት በተለይም “ግብፅ በዓባይ ውኃ ላይ ተፈጥሯዊ የባለቤትነት መብት የተረጋገጠ ነው” የሚለውን ስምምነት በመሻር የቀጣናው ሀገራት የጋራ መግባባት ከሌላቸው የትኛውም ስምምነት ተግባራዊ እንደማይኾን ለማሳያነት ይጠቅማል ብለዋል፡፡ በመኾኑም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ እየተደረገ ያለው ድርድር የቀጣናው ሀገራት ማገዝ እንደሚጠበቅባቸውም አስረድተዋል፡፡ በተለይም እንደ ኢጋድ ያሉ ተቋማት የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ለቀጣናው ሀገራት የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በመገንዘብ እገዛ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ ሌላው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የሚያስገኘው ጥቅም ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው፡፡ ይህ ማለት ከኢትዮጵውያን በተጨማሪ የቀጣናው ሀገራት ዜጎችም ወደ ህዳሴ ግድብ አካባቢ በመምጣት የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ይችላሉ፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ ፈረንሳይንና ጀርመንን ማየት በቂ መኾኑን ለአብነት አንስተዋል፡፡ እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አንዳርጋቸው ማብራሪያ በፈረንሳይና በጀርመን አጎራባች አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ወደ ፈረንሳይና ጀርመን በመሄድ ከተገነቡት ትልልቅ ፕሮጀክቶች በቋሚነትና በጊዜያዊነት ተቀጥረው ሀብት ንብረት እያፈሩ ነው፡፡
ረዳት ፕሮፌሰሩ በታሪክ፣ በስልጣኔ፣ በሕዝብ ቁጥር፣ በሰላም ማስከበር እና በቆዳ ስፋት ትልቅ ከኾነችው ኢትዮጵያ ሀገራት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በራሳቸው አቅም እንዴት መጨረስ እንዳለባቸው ተሞክሮ የሚወስዱበትም ነው ብለዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በአንድ ሀገር ያለውን ሀብት ለሌላው በመስጠት የሀብት መጋራት እንዲመጣም የሚያስችል መኾንኑ ገልጸዋል፡፡ በተለይም የወደብ ሀብት ያላቸው ሀገራት እየተገነባ ከሚገኘው የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል በመውሰድ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ይጠቅማል ብለዋል፡፡ እነሱም የወደብ አግልግሎት እንዲሰጡ በር ይከፍታል፡፡ ይህም ምሥራቅ አፍሪካን ወደ አንድ በማምጣት ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ተሰሚነት እንዲኖራት ያደርጋል ብለዋል፡፡
ግብፅና ሱዳን የዓባይን ውኃ ለረጅም ዓመታት ለብቻቸው ሲጠቀሙ ቆይተዋል ያሉት ምሁሩ “ውኃው የእኔ ብቻ ነው” ከሚል አስተሳሰብ በመውጣት የወንዙን ደኅንነት መጠበቅ፣ ዳርቻዎችን ማልማትና መንከባከብ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ሀገራትም እንደ አስዋን ግድብ ያሉትን ትልልቅ ግድቦች የመሥራት ልምድ ስላላቸው ተሞክሮአቸውን ቢያካፍሉ መልካም እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ በሚያስገኘው ቀጣናዊ ጠቀሜታ ሀገራት የትብብር አቅማቸውን ያጎለብታሉ ያሉት ምሁሩ የኢትዮጵያ ሕዝብም የተለመደውን ትብብር በማድረግ የህዳሴ ግድቡ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ተሳትፏቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ