
“በዓባይ ውኃ ላይ ግብጽና ሱዳን ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር የሚያራምዱት ፍትሐዊ ያልሆነ አቋም ነው” አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዓባይ ውኃ ላይ ግብጽና ሱዳን ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር የሚያራምዱት ፍትሐዊ ያልሆነ አቋም መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች የሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ ገለፁ።
አምባሳደር ኢብራሂም ግብጽና ሱዳን የሚከተሉትን የውኃ ፖሊስ መነሻ በማድረግ በሰጡት ገለጻ ሀገራቱ በዓባይ ውኃ የበላይነትን ለመያዝ በተለያዩ ጊዚያት ያደረጉትን እንቅስቃሴን አብራርተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጋር በመተባበር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የደረሰበት፣ የግድቡ የግንባታ አፈጻጸምና በግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ላይ ገለጻ ተደርገዋል።
ሀገራቱ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር የሚያራምዱት ፍትሐዊ ያልሆነ አቋምና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተካሄዱ የሶስትዮሽ ድርድሮችን በማስመልከት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች የሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሀገራችን የኢነርጂ ፍላጎት ያለውን ጠቀሜታ በማንሳት ግድቡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል። የግድቡ ደኅንነትን በተመለከተም ሶስቱም ሀገራት የተስማሙበት እንደሆነ አንስተዋል።
ለግድቡ የተደረገውን ሕዝባዊ ተሳትፎ በተመለከተም ለግድቡ ግንባታ የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ መቀጠሉንና እስካሁንም ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ድጋፍ መሰባሰቡን አቶ ሄኖክ ገልጸዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ ወቅት በግድብ ዙሪያ በአንድነት በመቆም የራሳቸውን አስተዋጽ እንዲያበርክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለተመቻቸው የውይይት መድረክ ያላቸውን ምስጋና ገልጸው፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉንም የሚመለከት የጋራ አጀንዳ ነው ብለዋል። የውስጥ አንድነትን በማጠናከር የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚደረገው የተለያየ ጫና ለመቋቋም ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙና ግንባር ቀደም ሚና እንደሚጫወቱም ገልጸዋል።
የፓርቲዎቹ አመራሮች ተመመሳሳይ መድረኮች መቀጠል እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m