የጀርመን መንግሥት የኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎትን ለማዘመን ሊሠራ ነው።

143

የጀርመን መንግሥት የኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎትን ለማዘመን ሊሠራ ነው።

ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎትና የጀርመን የኢኮኖሚ ጉዳዮችና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ፖስታ አገልግሎት ለማዘመን በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎቱን ለማዘመን የሚያስችል ጥናት ሲደረግ ቆይቶ ተጠናቅቋል።

በጥናቱ መሰረት የኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎትን በዲጂታል መንገድ ለማዘመን የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያስችል ውይይት እየተደረገ ነው።

የትግበራው አካል የሆነውን ስምምነት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚ ሐና አርዓያስላሴ እና በጀርመን የኢኮኖሚ ጉዳዮችና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኩል በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ቀዳሚ ጸሐፊ ሆልዝፉስ ካሌ ተፈራርመዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) የጀርመን መንግሥት የኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎትን ለማዘመን እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።

የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ በቴክኖሎጂ የሚደገፉ አገልግሎቶችን መስጠት አንዱ ሥራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው የፖስታ አገልግሎት ማዘመን ለኢ – ኮሜርስ (ኤሌክትሮኒክስ ግብይት) አገልግሎት ጅማሮ መደላድል ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሐና አርዓያስላሴ የፖስታ ዲጂታል ፍኖተ ካርታው በፍጥነት ወደ ትግበራ እንዲገባ የጀርመን መንግሥት ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ቀዳሚ ጸሐፊ ሆልዝፉስ ካሌ ከፍኖተ ካርታው ትግበራ በተጨማሪ በቀጣይ በተለያዩ ጉዳዮች በጋራ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

የፖስታ አገልግሎት መዘመን የፖስታ እና ጥቅል እቃዎችን ማድረስ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላትና በማዘመን ወደ ኢ -ኮሜርስ አገልግሎት ለሚደረገው ጉዞ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን እንደገለጹ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleኢትዮጵያ አስፈላጊውን ወታደራዊ ዝግጅት ማድረግና ሠርጎ ገቦችን መቆጣጠር የሚያስችል የደኅንነት መረብ መዘርጋት ይጠበቅባታል” ምሁራን
Next article“በዓባይ ውኃ ላይ ግብጽና ሱዳን ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር የሚያራምዱት ፍትሐዊ ያልሆነ አቋም ነው” አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ