“ከክልሉ ውጭ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ትርጉም ባለው መንገድ አልተሠራም” ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም

201
“ከክልሉ ውጭ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ትርጉም ባለው መንገድ አልተሠራም” ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ሦስት ዓመታት ሀገሪቱ ከገጠሟት አንኳር ችግሮች አንዱ በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀል ነው፡፡ በዚህም በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ተፈናቅለዋል እንዲሁም ንብረታቸው ውድሟል፡፡ ለዘመናት የነበረውን የአብሮነት እሴት ከመሸርሸሩም ባለፈ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቱ በቀላሉ የሚታከም አልሆነም፡፡ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀል ፈተናው እንደ ሀገር ቢሆንም በአማራ ክልል ላይ የፈጠረው ጫና ግን ከባድ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በአማራ ክልል በክልሉ ውስጥ እና ከክልሉ ውጭ በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ከ876 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከተፈናቃዮቹ መካከል 565 ሺህ የሚሆኑት ከክልሉ ውጭ ባሉት የኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በብዛት፤ ደቡብ እና ትግራይ ክልሎች ደግሞ በከፊል የተፈናቀሉ ናቸው፡፡
ለእነዚህ ተፈናቃዮች በየወሩ ከፌዴራል፣ ከክልሉ መንግሥት እና ከለጋሽ ማኅበራት ከሚሰበሰብ ሃብት አስቸኳይ የምግብ እና መሰረታዊ ፋላጎቶች ወጪ ይፈፀማል ያሉት የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ናቸው፡፡ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እና እየጨመረ መምጣቱ ደግሞ ለክልሉ መንግሥት ፈተና ሆኖበታል ብለዋል ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው፡፡
ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በቻግኒ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎች ወደ ቀያቸው በአጭር ጊዜ ይመለሳሉ ቢባልም አልተቻለም ነው የተባለው፡፡ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የአካባቢውን ሰላም በአጭር ጊዜ በማረጋገጥ ዜጎችን ወደ መኖሪያ ቀያቸው ይመልሳል የሚል እምነት ነበር ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም ትርጉም ባለው አግባብ ለውጥ ማምጣት ግን አልቻለም ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ ክረምት ሳይገባ ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ ተብሎ በመታሰቡ ምክንያት ለክረምት ወቅት በሚሆን አግባብ የቅድመ ዝግጅት ባለመሰራቱ ተፈናቃዮቹ ለማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ተጋልጠዋል ነው የተባለው፡፡ ተፈናቃዮቹ ከቀያቸው በመፈናቀላቸው ከደረሰባቸው ጉዳት በላይ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች በሚደርስባቸው እንግልት እና ስቃይ የበለጠ መጎዳታቸውን ነው ኮሚሽነሩ የገለፁት፡፡
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም ገለፃ ዜጎችን በዘላቂነት ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚደረገው ጥረት በክልሉ መንግሥት ብቻ የሚፈፀም አይደለም፡፡ “ከክልሉ ውጭ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ትርጉም ባለው መንገድ አልተሰራም” ያሉት ኮሚሽነሩ የፌደራል መንግሥት፣ ኮማንድ ፖስቱ እና ዜጎች የተፈናቀሉባቸው ክልሎች በበቂ ሁኔታ አልሠሩም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የጸጥታ ኀይሏን ያለማንም ይሁንታ እና ጣልቃ ገብነት የማሰማራት ሉዓላዊ መብት አላት” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next articleየመኸር ወቅት እርሻቸውን በዘር ለመሸፈን በቂ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን አሚኮ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡