
“ሰላም፤ እርጋታ እና የዜጎች ደኅንነት ለኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ እድገት ወሳኝ ናቸው”በአሜሪካ የኢትዮጵያ የሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ አማካሪ ምክር ቤት
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም፤ እርጋታ እና የዜጎች ደኅንነት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ፍትሐዊ እድገት ወሳኝ ናቸው ሲል በአሜሪካ የኢትዮጵያ የሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ አማካሪ ምክር ቤት ገለጸ።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ የሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ አማካሪ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የድጋፍ መግለጫ አውጥቷል።
ምክር ቤቱ በመግለጫው ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ሰቅዘው ከያዟት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ለመላቀቅ እና ለሁሉም ዜጎቿ አስተማማኝ የሆነ የልማት መሰረት ለመጣል የሞት-የሽረት ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ገልጿል።
የመንግሥት መዋቅር ክፉኛ በተዳከመበት ሁኔታ ላይ ኀላፊነቱን የተረከበው የለውጥ አመራር የተጋረጠበት ፈተና ቀላል አለመሆኑን እንደሚገነዘብ ጠቁሟል።
ይህ የለውጥ ሂደት እንዳይሳካ በውስጥና በውጭ የተደራጁ ግለሰቦች እና ቡድኖች “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ብሂል ሕዝብን በዘውግና በእምነት በመከፋፈል እና ሀገርን በመበታተን ላይ ያተኮረ ዕኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ከውጭ ጠላት መንግሥታት ጋር ተባብረዋል።
ምክር ቤቱ በመግለጫው እነዚህ ኃይሎች የሀገራችን ሕዝቦች በህይወታቸው ከፍተኛ ቦታ የሚሰጡትን ሃይማኖት ከመጠቀም አልፈው ከውጭ ኃይሎች እና መንግሥታት ጋር በማበር ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፈው ከመስጠት የማይመለሱ ናቸው ብሏል።
በአሁኑ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በምትመራበት ሕገመንግሥት መሰረት ስልጣንን ከምርጫ ውጭ የመያዝ ጥያቄ የሕገመንግሥት መሠረት የሌለውና ሕገ-ወጥ በመሆኑ፤ የሽግግር/የአደራ መንግሥትም ሆነ ሌላ አይነት የመንግሥትነት ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ፅኑ አምነታችን ነው ብሏል።
በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በማጤን፤ ምርጫውን፤ ነጻ፤ ፍትሐዊ፤ አሳታፊ፤ በተለይም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በማድርግ ሁሉም የመምረጥና የመመረጥ መብት ያለው ዜጋ መንግሥትን “በምርጫ ሂደት ከመመስረትና ከመምራት” ውጭ የምርጫ እቀባም ሆነ ሌላ አላስፈላጊ ጫና ማድረግም ሆነ ምርጫን ማወክ ምንም ፈይዳ የሌላቸው ዓሉታዊ ተግባሮች እንደሆኑ አስገንዝቧል።
የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ በዚህ አስቸጋሪ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ የፈተና ወቅት ሁኔታዎች በፈቀዱት መጠን የሚያደርገዉን ከፍተኛ ጥረት በመገንዘብና በመደገፍ፤ ማንኛውም ለኢትዮጵያና ለመላው ዜጎቿ በጎ የሚመኝ ግለሰብና ቡድን ይህንን የዲሞክራሲ ሂደት ማበረታታት አለበት ነው ያለው።
የሕዳሴ ግድብን የሁለተኛውን የውኃ ሙሌትም ሆነ ኢትዮጵያ በድንበሯ ውስጥ የሚገኘውን ውኃ የመጠቀም ሉዓላዊ መብት ያላት መሆኑን በማያሻማ ደረጃ በመደገፍ፤ የሱዳንና የግብፅ መንግሥታት ኢትዮጵያ ውኃውን እንዳትጠቀምና ሕዳሴ ግድብን ስኬታማ እንዳታደርግ የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጫና፤ ጣልቃ ገብነትና የውክልና ጦርነት አደጋዎች እንደሚገነዘብ ምክር ቤቱ ገልጿል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ባለችበት ነበራዊ ሁኔታ ይህ ብሔራዊ ምርጫ ሊኖረው የሚችለውን ሕጋዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ሀገራዊ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከምንወስደው ገንቢ ሚና ውጭ፤ በዘውግ፤ በእምነት፤ በግል ጥቅምና በሌላ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌለን መሆኑን እንገልጻለን ነው ያለው።
የኢትዮጵያን ሰላም፤ እርጋታና ፍትሐዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችንና ሂደቶችን ለማደናቀፍ የሚፈታተኑ ድርጊቶችን የመመከት የግልና የጋራ ብሔራዊ ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ መወጣት እንደሚያስፈልግም ጠቅሷል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ በሀገር ቤትና በውጭ ለሚኖሩ ወገኖች የሚከተሉትን የአደራ ጥሪዎች አቅርቧል።
1. በተለያዩ የሃይማኖት ጥያቄዎች ሰበብ ሕዝቦችን እርስ በእርሳቸው ለማጋጨት የሚደረጉ ሙከራዎችን በንቃት በመከታተል ከእነዚህ ድርጊቶች እንዲቆጠብና እንድንከላከል።
2. በማናቸውም ሃይማኖት ተከታዮች የሚነሱ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችና ጥያቄዎች አግባብነት ባለው ሁኔታ እንዲቀርቡ እና እንዲስተናገዱ እንዲደረግ፤ የሃይማኖት ተከታዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃይማኖት አስተዳዳሪዎች ወይም ኃላፊዎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ግዴታቸውንና ኀላፊነታቸውን በቅንነት
እንዲወጡ አደራ እንላለን።
3. መጪው ሀገራዊ ምርጫ የሀገራችንን የዲሞክራሲ መሠረት የምንጥልበት መሆኑን በመገንዘብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ሙሉ ድጋፍ የምንሰጠው መሆኑን እየገለጽን፤ ሁሉም አካላት በሕግ አግባብ በምርጫው በመሳተፍ እንዲሁም አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ ለምርጫው ስኬታማነት ድርሻውን እንዲወጣ አደራ እልላለን።
4. በዚህ አጋጣሚ፤ ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ሂደትም ሆነ ከምርጫው በኋላ የሚፈጠር ቅሬታ ቢኖራቸው በሕጋዊ ሂደትና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መንፈስ፤ የተቋማትን ገለልተኝነት ጠብቀው ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የዴሞክራሲ ሂደት ግንባታን እንዲያስተጋቡ እንጠይቃለን።
5. ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ መላው ኢትዮጵያውያን እንዳለፈው ከፍተኛ ጥረትና ድጋፍ ሁሉ በገንዘብም ሆነ የኢትዮጵያን በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም ሉዓላዊ መብት በልዩ ልዩ መንገዶች፤ ማኅበራዊ ሚዲያን ጨምሮ በመጠቀም ለዓለም መንግሥታት እና ሕዝቦች በማስገንዘብ ሙሌቱ እንዳይካሄድ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያከሽፉ ያልተቆጠበ ጥረት እንድናደርግ ብሄራዊና ሀገራዊ ግዴታችን እንድንወጣ አደራ እንላለን በማለት
በአሜሪካ የኢትዮጵያ የሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ አማካሪ ምክር ቤት ጥሪ ማስተላለፉን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ