በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት የተሠማሩ ማኅበራትን የገቢያ ትስስር በመፍጠር ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ።

162

በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት የተሠማሩ ማኅበራትን የገቢያ ትስስር በመፍጠር ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ።

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እንስሳና ዓሳ ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲና ማኅበራት በዶሮ እርባታ፣ በቀይ ሥጋ፣ በወተትና በዓሳ ሃብት ልማት ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ውጤታማነትን አስመልክቶ ምክክር አካሂደዋል።

የምክክሩ ዓላማ በእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ማኅበራት ሥራቸውን በዕቅድ እንዲመሩ ማስቻል፤ ከሸማቹ የገበያ ትስስር መፍጠር፣ የተሻለ ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ ማስቻልና መደገፍ እንደሆነ የአማራ ክልል የኅብረት ሥራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ ኀላፊ ኀይለልዑል ተስፋ ተናግረዋል፡፡
“አምራችና ሸማች ጥብቅ ትስስር መፍጠራቸው ለሀገር እድገት መሠረት ነው” ያሉት ኀላፊው ሁለቱ አካላት ትስስር የማይፈጥሩ ከሆነ ተጠቃሚ የሚሆነው ሕገ ወጥ ደላላው ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ሸማቹ የሚፈልገው የምርት ጥራት፣ አይነት፣ ብዛትና ጊዜን በአግባቡ መረዳት አምራቹን ስኬታማ ያደርጋል፤ ለዚህም በየወቅቱ መነጋገር እንደሚያስፈልግ አቶ ኀይለልዑል አስገንዝበዋል፡፡

የወተት ልማት ምርት ሸማቿ ወይዘሪት እልልታ ካሳ ውይይቱ ገዢና ሻጭን የበለጠ ሊያቀራርብ ይችላል ብላለች፡፡ በተለይ ገዢው ከየትኛው ሸማች መግዛት እንዳለበት አማራጮች እንዲኖሩት ያስችላልም ነው ያለችው፡፡

አቶ ዘየነው ዓለሙ የአውራምባ ማኅበረሰብ የገበሬዎችና ዕደ ጥበባት ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ማኅበራት ውጤታማ እንዲሆኑ የገበያ ትስስሩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት በክልሉ በእንስሳት ሀብት ልማት ለተሰማሩ ማኅበራት ድጋፍ ከሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ኤጀንሲ ማስፋፊያ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዳዊት ገዳሙ አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ በክልሉ በ15 ወረዳዎች የሚንቀሳቀስ ሲሆን በዶሮ ሀብት ልማት፣ በቀይ ሥጋ፣ በወተትና በዓሳ ሀብት ልማት ላይ ተደራጅተው ለሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ አቶ ዳዊት ተናግረዋል።
ማኅበራቱ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ሁሉ ኤጀንሲው የቴክኒክና ሙያ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ኀላፊው ጠቁመዋል፡፡
የተደራጁ ማኅበራትን ለማጠናከር የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ማድረግ፣ የተሻለ መኖን ማቅረብና ጤንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን መሥራት ኤጀንሲው ከፕሮጀክቶች ጋር የሚያከናውነው ተግባራት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‘’ፕሮጀክቱ በ2012 ዓ.ም በአማራ ክልል በ15 ወረዳዎች 1 ሺህ 350 የጋራ ፍላጎት ቡድን አቅፎ ነበር ሥራዉን የጀመረው፤ ከነዚህ ውስጥ የተሻለ አፈፃፀም ያሳዩ 31 ቡድኖች ወደ ደረጃ ሁለት ማኅበር ተሸጋግረዋል’’ ብለዋል፡፡
ወደ ደረጃ ሁለት ለተሸጋገሩ ማኅበራት ለእያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አቶ ዳዊት አስረድተዋል፡፡

በሥራ አፈፃፀማቸው ለተመረጡ ማኅበራት ድጋፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከሸማቹ ጋርም በማቀራረብ የገበያ ትስስር በሚፈጠርባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉን የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው ጠቅሰዋል፡፡

በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በውስን ሀብትና መሬት በርካታ የክልሉ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አቶ ዳዊት አመላክተዋል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት ብቻ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ነው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ያብራሩት፡፡

ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየሀገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድንና የማኅበረሰብ ደኅንነት ቅኝት አደረጃጀቶች ለማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት አጋዥ መሆናቸውን ሰላም ሚኒስቴር ገለፀ።
Next articleበሰሜን ሽዋ ዞን እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በተፈጠሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን እስከ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡