
የሀገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድንና የማኅበረሰብ ደኅንነት ቅኝት አደረጃጀቶች ለማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት አጋዥ መሆናቸውን ሰላም ሚኒስቴር ገለፀ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የገለልተኛ አማካሪ ቡድን እና የማኅበረሰብ ደኅንነት ቅኝት የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ የሚኒስቴሩ የሕግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ፍሬዓለም ሽባባው እንዳሉት ሰው በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ፖሊስ የተጣለበትን ሕዝባዊ ኀላፊነት በብቃት መወጣት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የተፈተነችው በጸጥታ ተቋማት እጦት ሳይሆን ሥርዓቱ የተዛባና አስተሳሰቡም ልክ ባለመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ወንጀሎችን፣ አላስፈላጊ የቃላት ልውውጦችን፣ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በከፍተኛ ሥነ ምግባርና በቁርጠኝነት መመከት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፖለቲካ፣ ከብሔር እና ከሃይማኖት አመለካከትና ከወገንተኝነት ገለልተኛ ፖሊስ ይፈልጋል” ያሉት ሚኒስትር ዲኤታዋ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ የፖሊስ ተቋም የመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ ገለልተኛ አማካሪ ቡድን እና የማኅበረሰብ ደኅንነት ቅኝት አደረጃጀቶች በተተገበሩባቸው አካባቢዎች ውጤታማ የጸጥታ ሥራ መኖሩን በመጥቀስም እንደ ሀገር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሀገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድንና የማኅበረሰብ ደኅንነት ቅኝት አደረጃጀቶች ለማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት አጋዥ መሆናቸውን በሚኒስቴሩ የወንጀል ማስከበርና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ተወካይ አምባዬ ወልዴ አብራርተዋል፡፡ አደረጃጀቱ በተተገበረባቸው የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የሐረሪ እና የሲዳማ ክልል አካባቢዎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጥሩ ውጤት መገኘቱን አመላክተዋል። በኀብረተሰቡና በፖሊስ መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሯል፤ በአጎራባች ወረዳዎችና ዞኖች አካባቢ ይፈጠር የነበረ የጸጥታ ችግር ቀንሷል፤ በፖሊስ ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎችም በአደረጃጀቱ እንዲሸፈኑ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
አደረጃጀቱን በማጠናከር ወጥነት ባለው መንገድ ከተተገበረ በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ማስቀረት እንደሚቻልም ነው የጠቀሱት፡፡ ለዚህም ክልሎች ውጤታማ በኾነ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ በክልሎቹና በከተማ አስተዳደሩ የታዩ ተሞክሮዎች፣ ጥንካሬዎችና ድክመቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመመስረት ግብዓት ይሆናሉ ተብሏል፡፡ በሁለት ሳምንታት ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ አደረጃጀቱ እንደሚመሠረትም አመላክተዋል፡፡ አደረጃጀቱ የሚመራው በፖሊስ ሲሆን ከማንኛውም ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ፍላጎት ውጪ በጸጥታ ጉዳይ ላይ ብቻ ለመሥራት ከ20 በላይ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ይሳተፉበታል፡፡
በአማራ ክልል ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የማኅበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ጀማል መኮንን እንዳሉት ሁለት አደረጃጀቶች በአማራ ክልል በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ቀደም ብሎ ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ ተግባራዊነቱም አበረታች ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ አደረጃጀቶቹ በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ ባለመደረጋቸው አሁንም በክልሉ የጸጥታ ችግሮች እየተፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይ አሠራሩን በማጠናከር የጸጥታ ችግሮችን ለመቀነስም በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ከዘጠኝ ክልሎችና ከአንድ ከተማ አስተዳደር የፖሊስና የጸጥታ ዘርፍ መሪዎች እየተሳተፉ ነው፤ ዛሬ የተጀመረው ውይይትም ነገ ቀጥሎ ይካሄዳል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
