
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከወራት በፊት የተጀመሩ እና ሕዝብን ያሳተፉ የጎርፍ አደጋ መከላከል ሥራዎች በአንዳንድ አካባቢዎች አለመጠናቀቃቸውን ገልጿል፡፡
የጎርፍ አደጋ መከላከያ ሥራዎቹ እስካሁን ያልተጠናቀቁት በጀት ለማፈላለግ በወሰደው ጊዜ በተፈጠረ መዘግየት እና በክረምቱ ቀድሞ መግባት መሆኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በነበረው ከፍተኛ የዝናብ መጠን በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋዎች ተከስተው ነበር፡፡ በአደጋው ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
በተያዘው የክረምት ወቅት ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ከፌዴራል እና ከክልሉ መንግሥት በተገኘ የበጀት ድጋፍ ከወረዳዎች ጋር በመተባበር ሕዝብን ያሳተፈ የጎርፍ አደጋ ቅድመ መከላከል ሥራዎች ከተጀመሩ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን በሰባት ዞኖች እና 20 ወረዳዎች የተጀመሩት የጎርፍ መከላከያ ሥራዎች ክረምቱ እየተቃረበ በመጣበት በዚህ ወቅትም አንዳንድ አካባቢዎች ላይ አልተጠናቀቁም ተብሏል፡፡
በክልሉ ለረጅም ጊዜ የጎርፍ አደጋ ምክንያት በሆኑት የጉማራ እና ርብ ወንዞች አካባቢ ሕዝብን ያሳተፈ የጎርፍ መከላከያ ሥራዎች ለማከናወን ከፌደራል መንግሥት 100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን ነው ኮሚሽነር ዘላለም የገለጹት፡፡
በክልሉ የጎርፍ አደጋ ስጋት ባለባቸው ሰባት ዞኖች እና 20 ወረዳዎች ላይ በወረዳዎቹ የበጀት ድጋፍ እና የክልሉ መንግሥት ባደረገው የ10 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ሕዝብን ያሳተፈ የጎርፍ መከላከያ ሥራዎች እየተካሄዱ ነው ብለዋል፡፡
ከፌዴራል እና ከክልሉ መንግሥት የተገኘውን የበጀት ድጋፍ ለማስፈቀድ በወሰደው ጊዜ እና በክልሉ በርካታ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ዝናብ ቀድሞ መከሰቱ የመከላከያ ሥራዎቹ ከተያዘላቸው ጊዜ ዘግይተዋል ብለዋል ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው፡፡
የጎርፍ መከላከያ ሥራዎቹን የሚፈፅሙት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መሆናቸውን ኮሚሽነር ዘላለም አንስተዋል፡፡ በዚህ ወቅት በርካታ ማሽነሪዎችን ወደ አካባቢዎቹ አስገብተው እየሠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የክረምት ወቅት የዝናብ ቅድመ ትንበያ ውጤት ባይደርስም ቀጣዩ ክረምት ከፍተኛ የዝናብ መጠን እንደሚኖረው አመላካች ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡ ለዚህ የሚመጥኑ የጎርፍ መከላከያ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የባለፈው ዓመት አይነት ጉዳት እንዳይደርስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን እና ከአቅም በላይ ቢሆን እንኳን ዜጎችን ከቀያቸው አውጥቶ ወደ ጊዜያዊ ማቆያ ለማስገባት በቂ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተደረጉ ነው ተብሏል፡፡
ኮሚሽነር ዘላለም የጎርፍ መከላከያ ሥራዎቹን የሚሠሩ የልማት ድርጅቶች የክረምት ወቅት እየገባ መሆኑን በመገንዘብ ሥራዎቹን በተቻለ ፍጥነት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡
ሕዝቡ እና በየደረጃው የሚገኘው የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር የጎርፍ አደጋ መከላከያ ሥራዎችን በትኩረት እንዲሠሩም ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
