
በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) “የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችች “በሚል መሪ መልዕክት በጀርመን በርሊን የኢፌዴሪ ኤምባሲ እና ፍራንክፈርት ቆንስላ ጀኔራል በጋራ አስተባባሪነት በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንቦት 08/2013 ዓ.ም 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።
በመድረኩ የኢፌዲሪ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጀርመን ለሚኖሩ የዲያስፖራ ወገኖች በዌብነር ማብራሪያ ሰጥተዋል። የግድቡ ግንባታ ሥራ በከፍተኛ የሀገራዊ ፍቅር ስሜት እየተከናወነ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ማንኛውም አይነት የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ሳትጎዳ የተፈጥሮ ኃብቶቿን ማልማቷን እንደምትቀጥልም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ሚኒስትሩ “ይህን የሀገር ኩራት በዘመናችን ታሪክ እንድንሠራበት አሻራችንን እንድናሳርፍበት ከዚህ ትውልድ መሆናችን ከእድለኝነትም በላይ ነው” ብለዋል፡፡
ግድቡን በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በቻሉት ሁሉ በመደገፍ ፍጻሜውን እውን ማድረግ እንደሚገባም ሚኒስትሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በጀርመን የኢፌዲሪ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ለሀገራዊ ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በተግባር የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በመሆን ለተገኙ የዲያስፖራ አባላት ምስጋና አቅርበው፣ የህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃትና ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ በረከቶች የሚኖሩት በመሆኑ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለዚህ ታላቅ ፕሮጀክት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በዌብነሩ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እያደረጉ ያለውን የነቃ የልማት ተሳትፎ እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፍራንክፈርት የሚገኘው የኢፌዴሪ ቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤት ቆንስል ጄኔራል ፈቃዱ በየነን በመወከል መልእክት ያስተላለፉት ወይዘሮ ኡብሀ መሐመድ የዘመናት ታሪክ ተቀይሮ ዐባይ ረግቶ ወገኖቹን ሊክስ የተቃረበ መሆኑን በመጥቀስ በተባበረ ክንድ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለዚህ ታላቅ የተቀደሰ ሥራ ሁሉም የበኩሉን እንዲያበረክት መጠየቃቸውን በጀርመን የኢትዮጵያን ኤምባሲ ጠቅሶ ኢብኮ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
