
የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች በዓል በዩኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርሶች እንዲመዘገብ እየተሠራ መሆኑን የፌዴራል ቅርስና ጥበቃ ባልስልጣን ገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔረሰብ አስተዳደሩ ልዩ መገለጫ የኾነው የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች በዓልን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ወካይ በማይዳሰስ የክብር መዝገብ እንዲመዘግብ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ነዋሪዎች፣ የፈረሶች ማኅበር አባላትና ምሁራን የሚያነሱትን ጥያቄ አሚኮ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወቃል። እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስና በዓሉን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ተቋም ለማስመዝገብ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎችን የያዘ ጥናት በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲና በብሔረሰብ አስተዳደሩ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ በትብብር ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በጉዳዩ ላይ የፌዴራል ቅርስና ጥበቃ ባልስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌውን አነጋግሯል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች በዓልን በዩኔስኮ ወካይ የክብር መዝገብ በማይዳሰሱ ቅርሶች በቋሚነት ለማስመዝገብ ሂደቱን የሚያስፈጽም ኮሚቴ ከተለያዩ ተቋማትና አደረጃጀቶች ከተውጣጡ አካላት መቋቋሙን ገልጸዋል።
የተቋቋመው ኮሚቴም መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግና የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት በዓሉን በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ቅድመ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ያግዛል ብለዋል።
አንድ ቅርስ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ማኅበረሰቡ እና መንግሥት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ያሳሰቡት ረዳት ፕሮፌሰሩ ጉዳዩም ለማኅበሩ ቋሚ ቦታ ከመስጠትና በሰፊው ከማስተዋወቅ ይጀምራል ብለዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ዘውዲቱ ወርቁ እንደተናገሩት ደግሞ የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማኅበር ከ57 ሺህ በላይ አባላት አሉት፤ በዓሉም በየዓመቱ በርካታ ታዳሚያንና አባላት በተገኙበት በእንጅባራ ከተማ ይከበራል ነው ያሉት።
እንደ መምሪያ ኀላፊዋ ገለጻ የሰባት ቤት የአገው ፈረሰኞች ማኅበር እሴቶችን በአግባቡ ጠብቆ ለ81 ዓመታት ተጉዟል፤ ማኅበሩ ከቀበሌ እስከ ዞን በአደረጃጀት የተጠናከረና በዞን ደረጃ 10፣ በወረዳ 70 እና በቀበሌ ደረጃ ደግሞ 550 የሥራ አስፈፃሚዎች አሉት። የበዓል አከባበሩን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ መምሪያው ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ነው ብለዋል።
የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማኅበር አባል ሻለቃ ግርማ መኮንን እንደተናገሩት ማኅበሩ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ በአካባቢያዊና ሀገራዊ ልማቶች ላይ በንቃት በመሳተፍ ከፍተኛ አበርክቶ አለው። የማኅበሩ አባላት በዓሉ እንዲታወቅ እያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል። የበዓሉ አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ተቋም ለማስመዝገብ የተጀመረው ሥራ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
አርቲስት ብርቱካን መለሰ በበኩሏ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የበርካታ ባሕላዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ባለቤት ነው። በአካባቢው የሚገኙ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊና ሌሎች ሀብቶችን ለትውልድ ለማቆየት በሙዚቃ ሥራዎቿ በማስተዋወቅ የበኩሏን ሚና እየተወጣች መኾኗን ተናግራለች። የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች በዓል አከባበር የብሔረሰብ አስተዳደሩ ልዩ መገለጫ በመኾኑ በዩኔስኮ ተመዝግቦ ታሪኩ ሳይበረዝ ለትውልድ ሊተላለፍ ይገባል ብላለች ።
ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
