
“በአንድ ህሊናና ሃሳብ በመገዛት ከተጋረጠብን ችግር ለመውጣት ጥረት ማድረግ ይገባናል” ብጹዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ነገሮች ከመበላሸታቸው በፊት በአንድ ህሊናና ሃሳብ በመገዛት ከተጋረጠብን ችግር ለመውጣት ጥረት ማድረግ እንደሚገባን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊና የድሬዳዋና ጅቡቲ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ አሳሰቡ፡፡
ብጹዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ በተለይ እንደገለጹት ስለ እናቶች፣ ሕፃናትና ስለአባቶች በአጠቃላይ ስለ ሰው ልጅ ሕይወት ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል። ሁሉም ለሰላም መስፈንና ለሰው ልጆች ደኅንነት መረባረብ ይኖርበታል፣ እየሆነ ያለው ትልቅ ትዕግስትን የሚጠይቅ፣ ለሀገርም ለሕዝብም ፈተና የሆነ ነገር ነው።
መንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ቅድሚያ መስጠት ለሚኖርብን ነገር ትኩረት እናድርግ ያሉት ብጹዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ፣ እንዲህ ዓይነት ነገር ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ እጅግ ከባድ በመሆኑ ለታሪክና ለሀገር ቅድሚያ እንስጥ ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበረሰብ፣ የሚዲያ አካላት፣ አክቲቪስቶችና መድረኩን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉ አካላት ሁሉ በተቻላቸው መጠን ሀገርን ለማዳን ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱም ጥሪ አቅርበዋል።
ሀገርና ሕዝብ ቅድሚያ ዋስትና ማግኘት አለባቸው፣ ሁሉም ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለሰላም መስፈንና ለሰብዓዊ መብት መከበር ነው፡፡ ሀገርንና ሕዝብን ማትረፍ የመጀመሪያ፣ ሌላው ሁሉ በሁለተኛነት የሚታይ እንደሆነም አስታውቀዋል። የሕዝብ ደኅንነትና ሰላም ለሕዝብም እንደ ሀገር ለመቀጠልም መሰረት በመሆናቸው መከበራቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ማስገንዘባቸውን የዘገበው ኢፕድ ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
