“አጀግኖ አሳደጋቸው፣ አክብሮ አኖራቸው፣ አሳምሮ ሸኛቸው”

415

“አጀግኖ አሳደጋቸው፣ አክብሮ አኖራቸው፣ አሳምሮ ሸኛቸው”

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግንነት በሕዝብ ከመወደድ ይጀምራል። ሕዝብ ከወደደህ ክብር ይሰጥሃል። ጀግና ማለት ጀብዱ ሠርቶ በሕዝብ ልብ ውስጥ መቀመጥ ነው። የጦር መሪ፣ ለሀገር ኗሪ፣ ለነፃነት ተከራካሪ፣ መልካም ሠሪ፣ ሩቅ አሳቢ፣ ወገን ሰብሳቢ ናቸው። ልብቻው አይፈራም። አልሞ መተኮስ፣ የጠላትን ምሽግ አባሮ ማፍረስ እንጂ፣ ፈርቶ ሽሽት አያውቁም።

የሀገሬው ሰው አብዝቶ ይወዳቸዋል፣ ሳይጠራጠር ያምናቸዋል። አድባር፣ መሪ፣ ወንዝ አሻጋሪ ይላቸዋል። ለእርሳቸውና ለሚወዳት ሀገራቸው ሲል አብሯቸው ዘምቷል። ጦር መክቷል። ደም አፍሷል። አጥንት ከስክሷል። የበጌ ምድር ጀግኖች ከጀግናው ጋር ስለፍቅርና ስለክብር ሲሉ በረሃ ወርደው፣ በጦር ተማግደው፣ ምሽግ ተራምደው ቀን አሳልፈዋል። አምነዋቸዋል አልከዷቸውም። ወደዋቸዋል አልጠሏቸውም። ተከትለዋቸዋል አልተመለሱም።

ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ አባደፋር እያሉ ስማቸውን ያነሷቸዋል። በጀግንነታቸው ይኮራሉ። በወንድነታቸው ይመካሉ። ምን አይነት መታደል ነው ከልጅነት እስከ ሞት ድረስ መታመን፣ ምን አይነት ወንድነት ነው ለሀገር ሲባል በረሃ መዋል። የወንድ ውኃ ልክ፣ የጀግንነት ሚዛን፣ የጥሩ ሰው ልሳን ናቸው። ጀግንነት ከአባታቸው የወረሱት፣ ለብሰው ያደጉት፣ የኖሩበት፣ ጀብዱ የሠሩበት ነው። የብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰን ወንድነት ሰው ሳይሆን ኦጋዴን ይመሰክራል፣ ቀብሪደሀር ይናገራል ጥይት እንደ ባቄላ የዘሩበት፣ ጠላትን እንደ ምጥ ያስጨነቁበት፣ እንደ ብቅል የደፉበት የኦጋዴኑ ነብር፣ የካራማራው ጀግና ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ ጠላት በአሻገር ሲያያቸው ገና ልቡ ይሸበራል፣ አስቀድሞ ይደነብራል። ምሽጉ በግርማቸው ይሰበራል። በኃይላቸው ዶግ አመድ ይሆናል። ኃይሌ አባ ነበር ይሏቸዋል ጓደኞቻቸው።

ሀገር ሲደፈር እንደነብር የሚቆጡ፣ ጋራ ለጋራ የሚያራውጡ ጀግና ናቸው። የሰሜን በጌምድር ሰው አጀግኖ አሳደጋቸው፣ አክብሮ አኖራቸው፣ አሳምሮ ሸኛቸው። ከጀግና አብራክ የተገኙ ናቸውና ጀግንነትን ወረሱ። እርሳቸውም ጀግና ሆኑና ታሪክ ሰሩ፤ ተከበሩም።

ከልጅንት እስከ ሞት ድረስ ኢትዮጵያ የሚሉት ጀግናው የጦር መሪ ድፍረታቸው ተጠልቶ፣ የአንድነት ሰባኪነታቸው ተትቶ፣ ወንድነታቸው ተረስቶ ጀግና በማይወዱት ባይከበሩም ታሪክ ግን አክብሯቸዋል፤ ሥራ ግን መስክሮላቸዋል። ከንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምረው ቆራጥ ወታደር በመሆን ሀገራቸውን ያገለገሉት ቆራጡ ወታደር ዚያድ ባሬን አሳፍረው ሀገራቸውን አስከብረው ታሪክ ከሠሩት ጀግኖች መካከል አንደኛው ናቸው።

ያ ዘመን አልፎ ሕወሃት መራሹ መንግሥት ስልጣን ሲረከብ፣ ሀገር እንደሚበትን አስቀድመው አውቀው ነበርና አምርረው ተቃወሙት፣ በረሃ ወርደው ተጋጠሙት። በዚያ የጀግንነት ጊዜ ታዲያ የሚወዳቸው የሀገሬው ሕዝብ አልተዋቸውም። አብሮ ዘመተ፣ አብሮ ታገለ እንጂ። በመንግሥት ያልተወደዱት ጀግና በሚወዷት ሀገራቸው መኖር ባይችሉም ስለሀገራቸው ግን ሳያስቡ ያደሩበት ጊዜ አልነበረም።

ሕወሃት እንኳንስ ከእነ ነብሴ ሞቼም እንድትነካኝ አልፈቅድም የሚሉት ጀግና ትግላቸው ፍሬ አፍርቶ ሕወሃት ሲወድቅ ሀገራቸው ገቡ። ዳሩ በሀገራቸው የመኖር ዘመናቸው ጥቂት ነበርና ሞት ቀደማቸው። ነብሴ በሀገሬ ትለፍ እያሉ የሚማፀኑት ጀግናው የጦር መሪ ልመናቸው ደረሰ። ፈጣሪ ፀሎታቸውን ሰማቸው፣ ጠላቶቻቸውን አጥፍቶ ለሀገር አበቃቸው። ስጋቸውም በመከራው ጊዜ ካልተለያቸው ሕዝብ መገኛ ታርፍ ዘንድ ወደዱ። በመከራው ዘመን አብሯቸው የነበረው ሕዝብም አክብሮ ተቀበላቸው። በወግና በማዕረጉ አዘነላቸው። አሳምሮ ሸኛቸው። የትግል አጋሮቻቸው ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌን ልብቻው አይፈራም። በጠላት ክንድ አይሸበሩም። ወደ ኋላ አያውቁም፣ ሁልጊዜም ወደፊት ብቻ ነው የሚሄዱት ይሏቸዋል። የኃይሌን እጅ መያዝ ተራራ እንደመግፋት ነው ይሏቸዋል። እርሳቸውም እጀኔን ከምሰጥ ጀግንነት እንዳስተማረኝ እንደ ቴዎድሮስ ጥይት እጠጣለሁ ይሉ እንደነበር ይነገርላቸዋል። ለዋይ ዋይታ አይደነግጡም። ተሸነፉ ሲሏቸው የሚያሸንፉም ነበሩ።

የቅርብ ዘመዳቸውና የትግል ጓደኛቸው ልባይ አበበ ኃይሌ ቤት የላቸውም። ቤታቸው ሀገርና የትግል ሥፍራ ነው ይሏቸዋል። ሰው አክባሪ፣ መልካም መካሪ፣ መልካም ተናጋሪ ናቸውም ነው የሚሏቸው። የእህታቸው ባልና የትግል አጋር ሻምበል ሲሳይ አየለ ኃይሌ ጀግና አዋጊ፣ ጀግና ተዋጊ፣ ጠላት ማራኪ ናቸው ነው ያሏቸው።

ወያኔ ሀገር አጥፊ ነው። ዛሬውኑ ተዋጋ ነገ ሀገር ስትበላሽ ይቆጭሃል ወያኔን ታገላት ይሉ እንደነበርም ነግረውናል። ለሀገር ዝመት፣ ለነፃነት ሙት ያልተደፈረች ሀገር እንደተቀበልክ ሁሉ ያልተደፈረች ሀገር አስቀጥል ይሉ ነበር ነው ያሏቸው። ኢትዮጵያን እግዚአብሔርም አይጥላትም። ሀገር ተጠናከር፣ ሀገርህን እንዳታስደፍር ይሉም ነበር።

የጀግንነት ባለቤት፣ የታሪክ መዝገብ ታላቁ ሰው ወደ ማይቀረው ሄደዋል። ይህ ጀግና ጀግንነት በሠሩበት፣ ታሪክ በፃፉበት ሀገርና ሕዝብ ፊት ከፍ ብለዋል።

“ጄኔራል ኃይሌ አሞተ ኩሩ፣
እንኳንስ ኖሮ ሞቱም ማመሩ” በሽኝታቸው ወገኖቻቸው ያሉት ነው። ታሪክ ሠርቶ መሞት እንደ መሞሸር ይቆጠራል። ስማቸው ተደጋግሞ ይጠራል። ጀግንነታቸው ይነገራል። ወኔ የሚቀሰቅሰውን ታሪካቸውን የሚያነሳው ሰው ሁሉ ጀግንነታቸውን እያነሳ ይፎክራል። ይሸልላል፤ታሪካቸውን ይዘክራል፤ ደግሞ በሌላ በኩል “በልክህ ጀግና ሥራ፣ ወንድነትህ ያስፈልገናል፣ ጀግንነትህ ይናፍቃናል፣ መኩሪያችን፣ መመኪያችን፣ ጥለህን አትሂድ” እያለ የሚንሰቀሰቀውም ብዙ ነው።

አጅባር ጀግናዋን አከበረች፤ልጇን ሸኘች፤ ጄኔራሉ በአጅባር ለቀብር ሳይሆን ለዘመቻ የሚሸኙ ይመስሉ ነበር። ለካስ ሞቶም ሰው ይኖራል፤ አልፎም ይከበራል፤ መመረጥ ለዓላማ መፅናት ምን አይነት መታደል ነው።

“አሙስ ወንዝ እንዴት ነው ጎንደርስ እንዴት ነው፤ አንድ ሰው ነበረ ይሄው ልንቀብረው ነው” ልብ የሚነካ የጀግኖች ቀረርቶ ነበር። ሞቶ መንገሥ። ምን አይነት መወደድ ነው ያን ያህል ሕዝብ መሰብሰብ፣ ምን አይነት ጀግንነት ነው ከሚዛን አለመዛነፍ። ምን አይነት ሥራ ነው በጥልቅ የሚያስወድድ። ያየ ይገረማል። የሰማ ጉድ ይላል። አፉ ለምስጋና ይዘጋጃል።

“ሰሜን በጌምድር የነብር አንበሳ
አለቀ አሉ ጀግና አንዳንድ ሲነሳ” ጀግናው ተነስተዋልና የአቅራሪው እንጉርጉሮ አንጄት ይበላል። የጀግናው ውኃ ልክ አስከሬን በክብር ከአጅባር ሜዳ ተነስቶ ወደ ደብረታቦር ደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሲሸኝ እጀባው ልዩ ነበር።

ስምን ከመሬት በላይ ትቶ ስጋን መሬት ውስጥ የመጣል ጊዜ ደረሰ። ስማቸውን በምድር ትተው፣ ዝናቸውን እንደ ተራራ አስቀምጠው፣ ጀብዳቸውን አብዝተው ጀግናው ግባተ መሬታቸው ተፈፀመ።

ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ ያረፉበት ቤተክርስቲያን እሳቸው ከልባቸው የሚወዱት፣ ሁልጊዜም የሚመኩበት፣ ፈለጉን የሚከተሉት አጼ ቴዎድሮስ ያሠሩት ነው። እሳቸውም በቀደመው ዘመን ዳዊት የሚደግሙበት ነበር። ሳይደክሙ ቆመው በጸለዩበት፣ ተኝተው ለዛላለም አረፉበት። በሰላም ይረፉ።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“አሁናዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከመንግሥት ፍጥነትን፣ ከፓርቲዎች ብስለትን እና ከሕዝብ ትዕግስትን የሚጠይቅ ነው” ዶክተር በዕውቀቱ ድረስ
Next article“በአንድ ህሊናና ሃሳብ በመገዛት ከተጋረጠብን ችግር ለመውጣት ጥረት ማድረግ ይገባናል” ብጹዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ