
የብርቱካን ፍራፍሬ በሽታ መድኃኒት መገኘቱ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በብርቱካን ፍራፍሬ ላይ የተከሰተው በሽታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ
ሲያደርግ ቆይቷል። በሽታው የብርቱካን ዛፍን በቁሙ እንደ እንጨት ያደርቀዋል፤ ፍሬ እንዳያፈራም ያደርገዋል። አቶ ማንደፍሮ
አስላከ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዕፅዋት በሽታ ተመራማሪ ናቸው። አቶ ማንደፍሮ ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ለዓመታት አርሶ አደሮችን
ፍሬ አልባ ሲያደርግ የቆየው የብርቱካን በሽታ መከላከያ መድኃኒትን በማግኘት የሀገር አለኝታነታቸውን አሳይተዋል። በብርቱካን
ዛፍ ላይ ይታይ የነበረው የበሽታው መንስኤ ሻጋታ (ፈንገስ) እንደሆነም ጠቁመዋል።
“የሰሜንና የምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ብርቱካንን የሚያጠቃ በሽታ ከ30 ዓመታት በፊት በመከሰት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ
በመስፋፋት ውድመት ሲያስከትል ቆይቷል” ብለዋል ተመራማሪው፡፡ በሽታው ሙሉ በሙሉ ዛፉን የማውደም አቅም እንዳለውም
አስረድተዋል። በሽታውን ለመከላከል የተለያዩ መድኃኒቶችን በመቀመም ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል ነው ያሉት። ለዓመታት
ሙከራ ሲደረግ እንደቆየ ያስታወሱት አቶ ማንደፍሮ “አሁን የተጠቀምናቸው መድኃኒቶች ሁሉም ውጤታማ ሆነዋል” ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘዉን የምርምር ውጤት በአትክልትና ፍራፍሬ ፓኬጅ ውስጥ በማካተት ተደራሽ ሊያደርገው
እንደሚገባም ጠቁመዋል። የተገኘው የብርቱካን ፍራፍሬ በሽታ መድኃኒት ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር ሲነፃጸር ለአካባቢ፣ ለሰውም
ሆነ ለእንስሳ ጉዳት የማያስከትል እንደሆነ አቶ ማንደፍሮ አስረድተዋል። መድኃኒቱ የብርቱካን በሽታን ብቻ ለመከላከል
እንደሚውልምና በፀረ ተባይና ፀረ አረም መሸጫ መደብር ስለሚገኝ አርሶ አደሮች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሚመራ ከወረዳና ከዞን የመጡ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለሙያዎች በሜጫ ወረዳ ቢኮሎ
ከተማ ሠርቶ ማሳያ ተገኝተው በብርቱካን በሽታ መከላከያ መድኃኒት ሙከራ ፍሬ ያፈራዉን የብርቱካን ዛፍ ተመልክቷል። ቡድኑ
የበሽታው መከላከያ የተደረገለትና መድኃኒት ባለማገኘቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰበትን የብርቱካን ዛፍ ንጽጽር ተመልክቷል።
አርሶ አደር ዘመናይ ብርሌ በቢኮሎ ከተማ ማንጎና አቮካዶን ያለማሉ። ብርቱካን መጠነ ሠፊ የሆነ በሽታ ስለሚገጠመው
በአትክልትና ፍራፍሬ ልማታቸው እንዳላካተቱት ተናግረዋል። በሽታው መድኃኒት ከተገኘለት ግን ብርቱካን ለማልማት ቁርጠኛ
እንደሆኑ ነው የተናገሩት።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ተስፋዬ አስማረ ዞኑ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ምቹ መሆኑን ተናግረዋል።
በብርቱካን ዛፍ ላይ የተከሰተውን በሽታ የሚያጠፋ መድኃኒት ለአርሶ አደሮች ታላቅ የምሥራች ዜና መሆኑን ተናግረዋል።
“ተመራማሪዎች ለብርቱካን በሽታ መድኃኒት እንዳገኙት ሁሉ በተለይ ለማንጎ በሽታም መፍትሔ ሊፈልጉለት ይገባል” ብለዋል።
መድኃኒቱንም አትክልትና ፍራፍሬ ለሚያለሙ ለዞናቸው አርሶ አደሮች ለማዳረስ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተስፋሁን መንግሥቴ የብርቱካን በሽታ መከላከያ መድኃኒት እንዲገኝ ቢሯቸው
ለተመራማሪዎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል። በሜጫ ወረዳ ቢኮሎ ከተማ የአትክልትና ፍራፍሬ ሠርቶ ማሳያ
መድኃኒቱን የተጠቀሙና ያልተጠቀሙ የብርቱካን ዛፎች ያላቸዉን ልዩነት ጎን ለጎን በማየት የመድኃኒቱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ
ተችሏል ብለዋል።
“በበሽታ ምክንያት ብርቱካን ከገበያዉ እየወጣ ነበር፤ አሁን ብርቱካን ከሌላ አካባቢ ነው ወደ ክልላችን እየገባ ያለው” ብለዋል
ምክትል ኃላፊው፡፡ አሁን የተገኘው መድኃኒት ለአርሶ አደሮች የምሥራች እንደሆነ ተናግረዋል። የምርምር ውጤቱ በሌሎች
ተመራማሪዎች ከተረጋገጠ በኋላ ቢሮው በፓኬጅ ውስጥ በማካተት ለአርሶ አደሮች የሚዳረስበትን መንገድ ያመቻቻል ብለዋል።
መድኃኒቱ ውጤት እስካስገኘ ድረስ በየወረዳው የሚገኙ የግብርና መዋቅሮች በችግኝ ጣቢያዎቻች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ
አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሮች ሙሉ ፓኬጁ ተቀርፆ ወደ ሥራ እስኪገቡ ድረስ በሽታ ያጠቃዉን ብርቱካን ከበሽታው መታደግ እንደሚችሉ
ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በማንጎና አቮካዶ ዛፎች ላይ የሚስተዋሉ በሽታዎችን ለመከላከል ቢሮው ከተመራማሪዎች ጋር እየሠራ
እንደሆነም አቶ ተስፋሁን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
