
የአከባቢውን ዘመናዊ የግብርና ሽግግር ማነቆዎች ለመፍታት እንደሚሠሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
ባሕር ዳር፡ መስከረም 7/2012 ዓ.ም (አብመድ) የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ስንዴን በኩታ ገጠም በማምረት ከሚታወቁ አካባቢዎች አንዱ የሆነውን ደብረ ኤልያስ ወረዳን ጎብኝተዋል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ ጥጃ ጎጥር እና ጉይ ቀበሌዎች ስንዴን በኩታገጠም የዘሩት አቶ አጉማስ ሽፈራው እና አቶ እናውጋው አምሳሉ ከሰብሉ ቁመና የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ በብተና እና በግል ፍላጎት ላይ ተመሥርተው ከሚዘሩት ይልቅ በኩታገጠም በየዓመቱ ዘርን በማፈራረቅ ዘመናዊ ግብርናን ተከትለው በመሥራታቸው እጥፍ ምርት ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ ለምርት ማመላለሻ ምቹ ማጓጓዣ ያለመኖር እና የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነር እጥረት የተዘራውን ያክል መሰብሰብ እየቻሉ አለመሆኑንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ለአካባቢው ዘመናዊ የግብርና ሽግግር ማነቆዎችን በየደረጃው እንደሚፈቱ ተናግረዋል።
የማጓጓዣ ችግሩን ለመፍታት ከደብረ ማርቆስ-ደብረ ኤልያስ- ተምጫ የአስፓልት መንገድ በቅርቡ ሥራ ጀምሮ ጥያቄያቸው እንደሚፈታ ተናግረዋል።
የምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም እና አዊ ብሔረሰብ ምርታማ ቦታዎችን የሚያስተሳስር መንገድ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የኮምባይነር እና የትራክተር አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ለግለሰቦች፣ ለዩኒየኖች እና ለባለሀብቶች የክልሉ መንግሥት ብድር ማመቻቸቱንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን አሰፋ በክልሉ በሰብል ከተሸፈነው 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 568 ሺህ በላይ ሄክታሩ በስንዴ ዘር የተሸፈ ነው ብለዋል።
በኩታ ገጠም ከተዘራው ስንዴ ከአንድ ሄክታር ከ26 እስከ 33 ነጥብ 5 ኩንታል ምርት ማግኘት የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የክልሉ ሰብል ሁኔታ 120 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት የታቀደውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል አቋም ላይ እንደሚገኝ ዶክተር ሰለሞን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ግርማ ተጫነ ከደብረ ኤልያስ