
ʺሊያጠፏት የተመኟት ያልቻሏት፤ ቅድስት ቤት”
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የማያልቅ መና የተቀመጠባት መሶበ ወርቅ ናት፡፡ የማይነጥፍ ጥበብ
የሚፈልቅባት፣ ተገፍታ የማትወድቅ፣ ተነግሮ የማያልቅ፣ በምንም የማይፋቅ፣ በወርቅና በአልማዝ የነጠረ ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡
ፈጣሪ ለምስክርነት ያስቀመጣት፣ በታዛዦቹ የሚያስጠብቃት፣ በጨለማ ዘመን፣ በሚያቃጥል እሳት መካከል ሳያስነካ
የሚያሳልፋት፣ ለምድር የፈቀደውን ሁሉ ለእርሷ የሰጣት ናት፡፡ የእርሱ መንፈስ በእርሷ ላይ አለ፡፡ እርሷም በእርሱ ኃይል ትኖራለች፡፡
በነገሯ ሁሉ እርሱን ታስቀድማለች፡፡ ዓለም በሚጨነቅበት ዘመን ስሙን ጠርታ፣ እጆቿን ዘርግታ የጭንቁን ዘመን ታልፋለች፡፡
የተጨነቀውን ዓለምም ታሳልፋለች፡፡ ኢትዮጵያ ድብቅ ሚስጥር፣ ወደር የማይገኝላት የማታረጅ እናት፣ እርስት፣ ጉልት፣ በረከትና
መድኃኒት ናት፡፡
በተቀደሰችው ምድር የተፈጠሩት ኢትዮጵያዊያን የተቀደሰውን አድርገው አለፉ፡፡ ለመተዳደሪያ ሥርዓት፣ ለማሸነፊያ አንድነት፣
ለመተሳሰሪያ ኢትዮጵያዊነት፣ ለመኖሪያ በረከት አስቀመጡ፡፡ የቀደሙት ኢትዮጵያዊያን በተፈቀደላቸው ቦታ፣ የተፈቀደውን ነገር
ያስቀምጣሉ፡፡ ያለ ምክንያት የሠሩት፤ ያስቀመጡት፣ ጥለው ያለፉት ነገር የለም፡፡ በምክንያት ኖሩ፣ በትጋት ሠሩ፣ በበረከት ከበሩ፣
የማያረጅ ነገር አኖሩ እንጂ፡፡ እንደ ውቅያኖስ ከሰፋው ታሪኳ ጨልፈው በቀመሱ ቁጥር የበለጠ ታሳሳለች፡፡ ታስደምማለች፡፡
በፍቅር ታስራለች፡፡ በናፍቆት ትጠራለች፡፡ በእርሷ ላይ የከበረ እንጂ በእርሷ ያፈረ የለም፡፡ በስሟ የዘመተ ያሸንፋል፤ ስሟን የጠራ
ያልፋል፤ በአፈሯ የተወለደ ይኮራል፤ ስለ ክብሯ የተዋደቀ ይከብራል፡፡ ክብሯ የገባቸው፣ ፍቅሯ ያሠራቸው፣ ሚስጥሯ የመራቸው
እኔን ከአንቺ በፊት እያሉ ይዋደቃሉ፡፡ እነርሱ ወድቀው ሀገር ያቆማሉ፡፡ ሃይማኖት ይጠብቃሉ፡፡ ማንነትን ያስከብራሉ፡፡
በየማደሪያችው በራቸውን የቆለፉት የባሕርዳር ነዋሪዎች በብዛት አልተነሱም፡፡ በጎዳናዎቿ የሚንቀሳቀሱት ተሽከርካሪዎች
አልበዙም፡፡ የቆለፋትን ጎጆ ከፍተው የወጡ ሰዎችም ጥቂቶች ናቸው፡፡ በዚያ ማለዳ መነሳቴ ወደ አንድ ታሪካዊ ቦታ ለመጓዝ
ነበር፡፡ በዚያ የተረጋጋ ማለዳ አካባውን እየቃኘሁ የጉዞ መነሻ ወደተባለበት ሥፍራ አቀናሁ፡፡ ነጫጭ የለበሱ ሰዎች በሰልፍ
ቆመዋል፡፡ ከሰዎቹ አጠገብ ለጉዞ የተዘጋጁ ተሽከርካሪዎች ተደርድረዋል፡፡ በእርጋታ የቆሙት ሰዎች ሳይጣደፉ ወደተደረደሩት
ተሽከርካሪዎች ይገባሉ፡፡ እኔም ለጉዞ ከተዘጋጁ ተሽከርካሪዎች መካከል በአንደኛው ገባሁ፡፡ በገባሁበት መኪና ውስጥ ከሞላው
ሰው ጮህ ብሎ የሚያወራ አይታይም፡፡ ሁሉም ተመስጦ ላይ ያሉ ይመስላሉ፡፡
ለጎዙ የሚያስፈልጉ ነገሮች ተጠናቀቁ፡፡ መኪናው ጉዞ ከመጀመሩ አስቀድሞ የሚደረሰው ጸሎት በኅብረት ተደረሰ፡፡ ከጥቂት
ደቂቃዎች በኋላ መኪናችን በባሕርዳር ደቡቧዊ ንፍቅ የተሠራውን መንገድ ይዞ መጓዝ ጀመረ፡፡ የረጋው ማለዳ ወደ መድመቅ ከፍ
እያለ ነው፡፡ በመኪናው መስኮት አሾልኬ ዓይኔ የደረሰበትን ሁሉ እየቃኘሁ ወደፊት ገሰገስን፡፡ የጭስ ዓባይ ፏፏቴን መሄጃ መንገድ
ወደግራ ትተን ወደፊት መጓዝ ቀጠልን፡፡ ልቤ ተንጠልጥሏል፤ አንድ ጉዳይ ለማዬት በመጓጓት፡፡ ጉዟችን ሩቅ እንዳልሆነ አስቀድሜ
ብሰማም ለማዬት ከነበረኝ ጉጉት የተነሳ ረጅም ሆኖብኛል፡፡ መኪናው በመጓዝ ላይ ነው፡፡ በቀኝና በግራ የተንጣለለው ምድር
በአሻገር ሲመለከቱት ለነብስ ረፍት ይሰጣል፡፡
መዳረሻችን በቀደመው አጠራር በጎጃም ክፍለ ሀገር በባሕርዳር አውራጃ በይልማና ዴንሳ ውስጥ ከመትገኝ ጥንታዊት ገዳም
ነው፡፡ ደብረ መዊእ ማርያም ገዳም እንተ ይእቲ ገባሪተ ኃይል ትባላለች፡፡ ከአዴት ከተማ ሳይደረስ ከመንገዱ በስተቀኝ በኩል
በእርሷ ስም በተሰዬመች የገጠር መንደር ውስጥ ነው የምተገኘው፡፡ መንደሯ ከተማ ለመሆን እየታተረች ያለች ትመስላለች፡፡
ተሽከርካሪዎቹ በመንደሯ ተደርድረው ቆሙ፡፡ ሰውም እየወረደ ወደ ተቀደሰችው ሥፍራ አመራ፡፡
ንጉሥ አፄ ልብነ ድንግል ነግሠውበት በነበረበት ዘመን በዚያ አካባቢ የሚኖሩ አንድ ታላቅ ካህን ነበሩ፡፡ ስማቸው ቄስ ተክለ
መድኅን ይባላሉ፡፡ ፈጣሪያቸውን የሚወዱ ፈጣሪም የሚወዳቸው ናቸው፡፡ በዚያ ዘመን የአካባቢው ሰው ራቅ ወዳለ ስፍራ እየሄደ
ቤተክርስቲያን ይሳለም ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ሩቅ መሆንም ምዕመናን እንዳሻቸው አምለኮት ለመፈፀም አይመቻቸውም ነበር፡፡
ይህን የተመለከቱት ታላቁ ካህን በዚያች አካባቢ ቤተ መቅደስ ማነፅ ፈለጉ፡፡ ቤተ መቅደስ ይሠራ ዘንድ ፈቃደ እግዚአብሔር
ደርሷል፡፡ በዚያ ዘመንም አቡነ ማርቆስ የሚባሉ ጳጳስ ነበሩ፡፡ እኒያ ካህንም ከጳጳሱ አስፈቅደው ቤተመቅደስ ሠሩ፡፡ በሠሯት ቤተ
መቅደስም አስባርከው ታቦተ ማርያምን አስገቡ፡፡ ይህ ዘመንም 1522 ዓ.ም ነበር፡፡ ካህኑ ተክለ መድኅን አራት ልጆች ነበሯቸው፡፡
ልጆቻቸውም ላእከ ማርያም፣ ክፍለ ማርያም፣ ሀብተ ማርያምና መቅደሰ ማርያም ይባሉ ነበር፡፡ መቅደሰ ማርያም የተባለችውን
ልጃቸውን ቄስ ዜና ለተባሉ ካህን አጋቧቸው፡፡ ሦስቱ ወንድ ልጆቻቸው ቀሳውስት ነበሩ፡፡ የልጃቸውን ባል ጨምሮ ከቤታቸው አራት
ቀሳውስት አገኙ፡፡ ከእራሳቸው ጋር አምስት ሆነው በአነፁት ቤተመቅደስ ቀደሱ፡፡
ሊቀ ኂሩያን በላይ መኮንን ታሪክ ዘደብረ መዊእ ማርያም ገዳም በሚለው መጻሕፋቸው የእኒያ ቄስ ልጆች ተባዝተው እየተተካኩ
ደብሯን እንደሚያገለግሉ አስፍረዋል፡፡ ዘመን ተተካ፡፡ በዙፋኑ ላይ አጼ ሱስንዮስ የንግሥና ስማቸው ስልጣን ሰገድ ተቀመጡበት፡፡
በእርሳቸው ዘመን የካቶሊክ ሚሲዮናውያን በኢትዮጵያ ነበሩ፡፡ ንጉሡም ከሚሲዮናውያን ጋር የጠበቀ ወዳጅት ነበራቸው፡፡
ከፖርቹጋል እንደመጡ የሚነገርላቸው ሚሲዮናዊያንም ንጉሡን ወደ ሃይማኖታቸው ሳቧቸው፡፡ የካቶሊክን ሃይማኖትንም ተቀበሉ፡፡
በዚያም ጊዜ ʺጽጌ ጽጌ ዘመስከረም ሱስንዮስ ንጉሠ ሮም” አሉ ብለው ሊቀ ኂሩያን በላይ መኮንን ጽፈዋል፡፡ ለሺህ ዓመታት በቤተ
መንግሥት ትልቅ ክብር የነበራት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች የንጉሡን አዋጅ ተቃወሙ፡፡
በመካከላቸው ጸብ ተነሳ፡፡ ሊቃውንቱም እየተሰባሰቡ የንጉሡን አዋጅ ተቃወሙ፡፡ ሊቃውንቱ ከተቃወሙባቸው ሥፍራዎች መካከል
አንደኛዋ ደብረ መዊእ ነበረች፡፡ በደብረ መዊእ እልፍ ሊቃውንት ተሰባስበው ነበር፡፡ እኒያ ሊቃውንት በጉባኤያቸው ላይ ʺለሰው
ከምናደላ ለእግዚአብሔር እናድላ፣ የክርስቶስን ፍቅር የሚከለክለን፣ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማነው? መራብ ነው? ሰይፍ ነው?
መራቆት ነው? ስደት ነው?” ይሉ ነበር ይባላል፡፡ የተቃዎሙት ሊቃውንትም በተሰባሰቡበት እንዲገደሉ ተደረጉ ይላሉ ሊቃውንቱ፡፡
በዚያም ቀን የሞቱት ሊቃውንት በሺህዎች ይቆጠሩ ነበር ይባላል፡፡ ሊቀ ኂሩያን በላይ መኮንን ከሰባት ሺህ ያላነሱ ህይወታቸው
ማለፉን ጠቅሰዋል፡፡ በዚያ ቀን የፈሰሰው ደም ʺእስከ ውኀዘ ደሞሙ ከመ ማየ ክረምት” ደማቸው እንደ ክረምት ውኃ ፈሷል ይላሉ
አበው፡፡
ይህም ዘመን አለፈ፡፡ ሱስንዮስ ዙፋናቸውን ለልጃቸው ለአቤቶ ፋሲለደስ አስረከቡ፡፡ ፋሲለደስም ʺወአግብዕ ደሞሙ ለስማዕት”
የሰማዕትነት ደማቸውን መለሰ ይባላል፡፡ ይህም በመግደል ሳይሆን የሚሹትን በመፈጽም እንጂ፡፡ ንጉሡ ፋሲለደስም በደብረ
መዊእ ሰማዕትነትን የተቀበሉትን ሊቃውንት ለማሰብ በመስከረም 21 ቀን የብዙኃን ማርያም እንዲከበር በሊቃውንት ጉባኤ
አስወስነው አዋጅ አስነገሩ፡፡ ሊቃውንቱም በመስከረም 21 ቀን ሰማዕታቱን ሲያስቡ ʺየአካለ ክርስቶስ እድምተኞች የሆናችሁ
የመሲሕ ክርስቶስ ሰማዕታት ሆይ በብርሃን ሰሌዳ ላይ በኪሩብ ሥዕል አምሳል የሕይወት መጽሐፍ ምስጢሩ ለተጻፈ የስም
አጠራራችሁ ሰላምታ ይገባል፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ምእመናን የድል አምባ ወደ ምትባል ደብረ መዊእ ማርያም እየተመሙ መጡ፤
ተሰበሰቡ፡፡ ሰማዕትነትንም ተቀብለው በመንግሥተ ሰማያት ተድላ ደስታን አደረጉ” ይሏቸዋል ሲሉ ሊቀ ኂሩያን በላይ መኮንን
ጽፈዋል፡፡
ሌላ ዘምንም መጣ፡፡ አጼ ቴዎፍሎስ ስመ መንግሥታቸው አፅራር ሰገድ ነገሱ፡፡ እሳቸውም በወንድማቸው በአድያም ሰገድ ሞት
ይቆጩ ነበር፡፡ አድያም ሰገድ ኢያሱ በግፍ ተገድለዋል ይባል ነበርና፡፡ አድያም ሰገድ ኢያሱን በግፍ እንዲገደሉ ካስደረጉ መካከል
አንደኛው ደጅ አዝማች ዳርምን የሚባሉ ሰው ነበሩ፡፡ አጼ ቴዎፍሎስም ገዳዮችን ለመቅጣት ጦራቸውን ይዘው ተንቀሳቀሱ፡፡ ደጅ
አዝማች ዳርምን እና አጼ ቴዎፍሎስ በደብረ መዊእ ተጋጠሙ፡፡ የአጼው ኃይል አየለ፡፡ ደጅ አዝማች ዳርምን በትሩን ስላልቻሉት
ጥቂት ተከታዮቻቸውን ይዘው ደብረ መዊእ ውስጥ ገቡ፡፡ ንጉሡም ዳርምን የተደበቁበትን ደብር በጥይት መቱት፡፡ በባሕር ዳር
ደብረ ፀሐይ ሰላም አድርጊው ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲን መምህርና የደብረ መዊእ ደቀ መዝሙር መምህር ያረጋል ተዋቸው
እንደነገሩኝና ሊቀ ኂሩያንም እንደጻፉት ቤተክርስቲያኗ በጥይት ስትመታ ʺወኮነት ማየ ቆሪረ” እንደ ውኃ ቀዝቅዛ ልትቃጠል
አልቻለችም፡፡ ንጉሡም ተገረሙ፡፡ ʺእናቴ እመቤቴ ሆይ ይህ ቤት ቢቃጠልና ጠላቴ ቢጠፋልኝ ውስጡን በደብተራ ውጩን በኖራ
እሠራሉ” አሉ፡፡ ፀሎታቸውም ተሰማ፡፡ ሁለት ጊዜ ተተኩሶባት አልቃጠል ያለችው ደብር ተቃጠለች፡፡
ሊቃውንቱ ደብሯ በፈቃድ ተቃጠለች ይላሉ፡፡ ለዚህም ስትቃጠል ʺእንዘ የዐውድዋ አርጋብ ንጹሓን ወአዕዋፍ ጽዕድዋን” ነጫጭ
ወፎችና ርግቦች ከበዋት ከቤተመቅደሱ አጠገብ ከሚገኘው ወይራ ዛፍ ላይ አረፈች፡፡ እርሷም በደብሯ ውስጥ የነበረውን ሁሉ
አውጥታው ነበር፡፡ ቃጠሎው በፈቃድ ነበርና የተቃጠለባት ነገር አልነበረም፡፡ ያን ወይራም አሳይተውኛል፡፡ ንጉሡ ያሰቡት ተሳካ፡፡
ተግባራቸውን ፈፀሙ፤ ስለታቸውንም አደረጉ፡፡ ያም ዘመን 1700 ዓ.ም ነበር፡፡ ንጉሡ ባዩት ነገር ሁሉ ተገርመው በማንም ዘመን
ያልታዬ ድንቅ ታምዕር አየሁ አሉ፡፡ ለቤተክርስቲያኗም የሚገባትን መባ ሁሉ ሰጡ፡፡ መጠሪያዋንም የድል አምባ ሲሉ ʺደብረ
መዊእ” ሲሉ ሰየሟት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ታቦቷ ገባሪተ ኃይል ትባላች፡፡ ቤተክርስቲያኗን በ1700 ዓ.ም መጀመሪያ ገደማ
ተገደመች ይባላል፡፡ በገዳሟ ውስጥ ደናግል ዲያቆናትና መነኮሳት ብቻ እንደሚቀድሱባትም ሰምቻለሁ፡፡
ዘመን የተሸገሩ ረጃጅም ዛፎቿ ውበትን ያላበሷት ይህች የሊቃውንት መፍለቂያ አያሌ ታሪክ ይዛለች፡፡ መንፈስን በሚያድሰው አጽዷ
ውስጥ ሲመላለሱ የሚያሸቱት፣ የሚያዩት፣ የሚዳስሱት ሁሉ እጽብ ያሰኛል፡፡ በዚህች ደብር ውስጥ ሌላ አንድ ታሪካዊ የወይራ ዛፍ
አለ፡፡ ያ ወይራም የእቴጌ ጣይቱ ወይራ ይባላል፡፡ እቴጌዋ የተወለዱበት ሰሜን ቤጌምድር ጠቅላይ ግዛት ደብረ ታቦር ከተማ ነው፡፡
በዚያም ሲኖሩ አባታቸው ሞቱባቸው፡፡ እናታቸውም ባል አግብተው ወደ ጎጃም ሄዱ፡፡ እቴጌዋም ወደ ደብረ መዊእ ይሄዱ ነበር፡፡
በደብሯም ከሚገኝ ትልቅ የወይራ ዛፍ ሥር እየተቀመጡ ዳዊት ይደግሙ ነበር፡፡ ዳዊትም የተማሩት በዚያች ቤተክርስቲያን ነበር፡፡
አካባቢው ጥቅጥቅ ያለ ደን ነበር፡፡ ጣይቱ ወደዚያች ደብር ሲያዘወትሩ ያይዋቸው አንድ አባትም ʺአንቺ ቁንጅናሽ መልካም
በጸሎትሽ ብትገፊበት ትልቅ ፀጋ ታገኚ ነበር፡፡ ይሁንና መልካም ነሽና የሸዋው ንጉሥ አንቺን ያገባሻል” ብለዋት ተሠወሩ ይላሉ
አበው፡፡ የተባለው ደረሰ፡፡ የሸዋው ንጉሥ እቴጌዋን አገቡ፡፡ እቴጌዋም ዳዊት የደገሙባት፣ ትንቢት የሰሙባት ቤታቸው ነበረችና
ገዳሟን አብዝተው ይወዷት ነበር፡፤ በዘመናቸውም አያሌ ስጦታዎችን ሰጥተዋል፡፡ የእሳቸው ስጦታም በገዳሟ ሙዜም ውስጥ
ይገኛል፡፡ የእርሳቸው ወይራ የሚባለው ጥንታዊ ዛፍም እስከ ግርማው አለ፡፡
ዘመን ዘምንን ተክቶ የአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ደረሰ፡፡ የጣልያን ወራሪዎችም በደብረ መዊእ አካባቢ እየተሰባሰቡ
የሚያስቸግሯቸውን አርበኞች ለማጥፋት ሲሉ ገደሟን ማቃጠል ፈለጉ፡፡ በተዋጊ አውሮፕላን በቦንብ ይመቷት ጀመር፡፡ ቦምቡ ግን
ማቃጠል አልቻለም፡፡ ደብዳቢው አውሮፕላንም ከገዳሟ አጠገብ ተከሰከሰ፡፡ የአውሮፕላኑ ስብርባሪም በቤተ መዘክሯ ውስጥ
ይገኛል፡፡ ደብረ መዊእ ባሳየችው ታምር አርበኞች የበለጠ እየተበረታቱ ሄዱ ብለውኛል መምህር ያረጋል፡፡
በገዳሟ ውስጥ እልፍ ሊቃውንት ወጥተዋል፡፡ ደብረ መዊእን የሊቃውንት መዝሪያ ማሳ ይሏታል፡፡ በገዳሟ ውስጥ የብራና
መጻሕፍት ከነሐስ፣ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ንዋዬ ቅድሳት፣ በብርና በወርቅ ያጌጡ አልባሳትና ሌሎችም ታሪካዊና መንፈሳዊ
ቅርሶችን ይዛለች፡፡ በዚያች ገዳም ውስጥ መጽሐፈ መድኃኒት የተሰኘ ብቸኛ መጽሐፍ መኖሩን መምህር ያረጋል ነግረውኛል፡፡
ገደሟ የቀድመው መተዳደሪያዋ ስለሌላት ድጋፍ የምትሻ መሆኑንም ሰምቻለሁ፡፡
ረጃጅም ዛፎች ምስጋና እንደሚያደርሱ ሁሉ በነፋስ እየተገፉ ያረግዳሉ፣ አዕዋፋት በዛፎቹ ላይ አርፈው ይዘምራሉ፣ በገዳሟ አጸድ
ውስጥ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ለአገልግሎት ሲፋጣኑ ይታያሉ፣ በረጃጅም ዛፎቹ ስር ቆመው ፈጣሪያቸውን የሚለምኑ ምእመናንም
ይማፀናሉ፡፡ የዛፎቹ እንቀስቃሴ፣ የእዕዋፋት ዝማሬ፣ የገዳሙ ግርማ ልብን በተመስጦ ያጠፋል፡፡ ምን አለበት ዘመኔ ሁሉ በዚህ
በሆነ ያስብላል፡፡ የአጸዱ ማዕዛ ሊገልጹት የማይችሉት ሐሴት ይሰጣል፡፡ ልቤን የማላውቀው ደስታ ሲመላው ተሰማኝ፡፡ ከአጸዱ
ውስጥ መውጣት አስጠላኝ፡፡ ዳሩ መውጣት ግድ ነው፡፡ በረጃጅም ዛፎች ስር ለስር አድርጌ ወደ ምሥራቅ ንፍቅ አቀናሁ፡፡ እግሬ
ከአጸዱ ውጭ ሄዷል፡፡ ልቤ ግን በአጸዱ ውስጥ በረጃጅም ዛፎች ጥላ እንደተጠለለ ነው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
