
የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ከ945 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የአጣዬና አካባቢው መልሶ ማቋቋም
ግብረ ኀይል ገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎችን
በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም እና የወደሙ ቤቶችን ለመገንባት 945 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የአጣዬና አካባቢው
መልሶ ማቋቋም ግብረ ኀይል አስታውቋል።
ግብረ ኀይሉ ዛሬ በሰጠው መግለጫ መልሶ በማቋቋሙ ሂደት ሁሉም ዜጋ የሚችለውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፏል።
ግብረ ኀይሉ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች በተከሰተ ግጭት ብቻ ከ300
ሺህ በላይ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ በርካቶችም ህይወት እና ንብረታቸውን አጥተዋል።
በደረሰው ጥቃት ቤታቸው የወደመባቸው ወገኖች የክረምቱን ወቅት ሊቋቋሙት በሚችሉበት ደረጃ የሚገኙ ባለመሆናቸው ካለፉት
አራት ሳምንታት ጀምሮ በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የሚመራ ግብረ ኀይል ተቋቁሞ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም
እየተሠራ እንደሚገኝ በመግለጫው ተመላክቷል።
የአጣዬና አካባቢው መልሶ ማቋቋም ግብረ ኀይል ሰብሳቢ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ
እንዳሉት ኢትዮጵያውያን ለሀገር ሉዓላዊነት በጋራ መሥዋእትነት ከፍለዋል። ይሁን እንጂ ባለፋት ሦስት ዓሥርት ዓመታት በሀገሪቱ
የተዘራው የጥላቻ ዘር ዜጎች በማንነታቸው የጥቃት ሰለባ ሆነዋል።
የተለያዩ አደረጃጀቶችን በየደረጃው በማቋቋምም በአዲስ አበባ፣ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የኀብረተሰብ ክፍሎችን እና በውጭ
የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ለቤት መሥሪያ የሚያገለግሉ ቁሳቁስ የማሰባሰብ ሥራ
እየተከናወነ እንደሚገኝ ምክትል ርእሰ መስተዳደሩ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ ገልጸዋል።
የሀብት አሰባሳቢ ግብረ ኀይሉ ዝርዝር የሥራ እንቅስቃሴውን እና አጠቃላይ የተሰበሰበውን የሀብት መጠን ባሥቀመጠው የጊዜ
ሰሌዳ መሠረት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም ተጠቅሷል።
በሁለቱ ዞኖች የተፈናቀሉ ዜግችን በጊዜያዊነት ለመደገፍ እና በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም እንዲሁም ከ6 ሺህ 600 በላይ
የወደሙ የገጠር እና የከተማ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት 945 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ በመግለጫው ተጠቅሷል።
የሚፈለገውን ገንዘብ ለመሰብሰብ ግብረ ኀይሉ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን፣ የፌዴራል መንግሥት፣ የፌዴራል
ተቋማት፣ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ዓለም አቀፍ የረድኤት
ድርጅቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
በዜጎች ላይ እየደረሰ የሚገኘውን መፈናቀል ለማስቆምም ኢትዮጵያዊያን በጋራ እንዲታገሉ ግብረ ኀይሉ ጠይቋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m