
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በአዊኛ ቋንቋና ሥነጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢ ነዋሪዎች፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ ምሁራን፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የአዊኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ሥርዓተ ትምህርት ማበልጸግ አውደ ጥናት አቅርቧል።
የአዊኛ ቋንቋ ትምህርት በአንደኛ ደረጃ በ1989 ዓ.ም መሰጠት ተጀምሯል፡፡ በ1997 ዓ.ም ደግሞ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በራዲዮ ፕሮግራም መተላለፍ እንደጀመረና በ2001 ዓ.ም ደግሞ በዲፕሎማ ደረጃ ትምህርት መሰጠት የተጀመረ መኾኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የማኀበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አራጋው ደለለ ለተሳታፊዎች ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል። በጥናታዊ ጽሑፋቸው ዩኒቨርሲቲው የአዊኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ በመጀመሪያ ዲግሪ መስጠቱ በቂ የሰው ኀይል ለማፍራት ያግዛል፤ ለጥናትና ምርምር ያግዛል ብለዋል፡፡ አሁን በመጀመሪያና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዊኛ ቋንቋን እያስተማሩ የሚገኙ መምህራንም የቋንቋ ሳይሆን የሒሳብና መሰል የትምህርት ክፍል ተመራቂ መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ይህንን ችግር ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።
በአውደ ጥናቱ የተሳተፉት የአካባቢው ነዋሪ አቶ ያዘው ዘለቀ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በአዊኛ ቋንቋ በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ መሰጠቱ ለቋንቋው እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል ብለዋል። “ይህንን በማየቴም እጅግ ደስ ብሎኛል” ነው ያሉት አቶ ያዘው። መርኃ ግብሩ እንዲሳካ ለሠሩ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ዋልተንጉሥ መኮንን (ዶ.ር) እንደተናገሩት በአዊኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ለመስጠት ሥርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶ መቅረቡ ትልልቅ አባቶች በቃል ደረጃ ያቆዩትን እውቀት ሰንዶ ለትውልድ ለማስተላለፍ ይጠቅማል።
የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃው ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል። በተለይም ትልልቅ አባቶች ሲያልፉ እውቀቱም አብሮ ሊጠፋ ስለሚችል ቋንቋውን ለትውልድ ለማስተላለፍ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በሥርዓት ተሰንዶ ሊቀመጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአዊኛ ቋንቋና ሥነጽሁፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ለመስጠት የተቀረጸው ሥርዓተ ትምህርትም ቋንቋን፣ ሥነ ጽሑፍን፣ የባህል ጥናትንና ሥነ ተግባቦትን የያዘ በመኾኑ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
የአዊኛ ቋንቋ በሥነ ጽሑፍ ረገድ የሚፈለገውን ያክል ደረጃ ባለመድረሱ ዩኒቨርሲቲው ለመነሻ የሚኾኑ ሥነ ቃሎችን መሰብሰብ እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል።
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት መምህር አደም ጫኔ (ዶ.ር) እንደገለጹት ትምህርት የሁሉም ነገር ቁልፍ ነው፡፡ በመኾኑም በአዊኛ ቋንቋና ሥነጽሑፍ በመጀመሪያ ዲግሪ መስጠት መጀመሩ የአካባቢው ማኀበረሰብ ባህሉንና ቋንቋውን ለማሳደግ ይጠቅመዋል ብለዋል።
በቋንቋ ዙሪያ ሰፊ ሥራዎችን ለመሥራት ደግሞ የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ወሳኝ መኾኑን ጠቁመዋል። ሥርዓተ ትምህርቱም እውቀት ያላቸው ዜጎችን ለማፍራት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያስገኛል ነው ያሉት። ዞኑም የማኀበረሰቡን ስነ ቃላዊ መረጃዎችን በመሰብሰብ ዩኒቨርሲቲውን ማገዝ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ሥነ ጹሁፍ የባሕል እሴቶችን አጉልቶ ለማውጣት ይጠቅማል ያሉት ዶክተር አደም ሀገር በቀል እውቀትን ለልማት ለማዋልም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያርግም አስገንዝበዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ይዞት የቀረበው የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ በርካታ መልካም ነገሮች ያካተተ ነው ብለዋል፡፡
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት አዕምሮ ታደሰ (ዶ.ር) በአዊኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ለመስጠት የተካሄደው የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ከብዙ ተቋማት ልምድ ተወስዶበት የተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዊኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚያስተምር መምህራንን ለማፍራት ዩኒቨርስቲው ይሠራል ብለዋል።
የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ሲደረግ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል ያሉት ዶክተር አዕምሮ በሴኔት በማጸደቅ ለከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በማቅረብ የሳይንሰና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እውቅና ከሰጠው በኋላ በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ይጀመራል ብለዋል።
ዘጋቢ :- አዳሙ ሽባባው – ከእንጅባራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m